በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአብያተ ክርስቲያኑ ቃጠሎና የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ መልስ


ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ

ሰሞኑን በበርካታ አብያተ ክርስቲያን ላይ እሳት የለኮሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ማኅበራዊ ውጥረት ለመፍጠር እየተንቀሣቀሰ መሆኑን በመግለፅ የከሰሱት አንድ ብዙም ታዋቂነት የሌለው ሙስሊም አክራሪ ቡድን መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስታወቁ፡፡

በአካባቢው ያለው የፀጥታ ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው የገለፁት አቶ መለስ በኢትዮጵያ ውስጥ በሰሜን አፍሪካ ሃገሮች እየታየ እንዳለው ሕዝባዊ አመፅ ሊፈጠር እንደማይችል አመልክተዋል፡፡

በሥልጣን ላይ ሃያ ዓመታትን ያስቆጠረውን ኢሕአደግን ለመጣል በውስጥም በውጭም እንቅስቃሴዎች እንደሚደረጉ እንደሚያውቁ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ አምባገነን አገዛዞችን ለማስወገድ እንደገነፈለው ዓይነት ሕዝባዊ ቁጣ በኢትዮጵያ የመከሰቱን ጉዳይ ውድቅ አድርገውታል፡፡

"የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ - አሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ - ያንን ሊያመጡ የሚችሉ ሁኔታዎች የሉም፡፡ ያ ማለት ግን አንዳንድ ሰዎች አይሞክሩም ማለት አይደለም፡፡"

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብዛኛው የእሥልምና ዕምነት ተከታይ በሆነበት በአንድ የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በአሥሮች የሚቆጠሩ አብያተ ክርስቲያን የመቃጠላቸው ጉዳይ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል፡፡ ብርካታ ወጣቶች ችቦ ይዘው የአምልኮ ቤቶችንና የአማንያን መኖሪያዎችን ሲያቃጥሉ እንደነበር ክርስቲያኖቹ ሲናገሩ ሰንብተዋል፡፡

ይንን አድራጎት እየፈፀመ ያለው ኽዋሪጃ የሚባል አንድ አናሣ የእሥልምና አክራሪ ቡድን ነው ብለውታል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

"በዚህ የተለየ ጉዳይ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ውስጥ በሁሉም የዕምነት ተቋማት ውስጥ አንዳንድ ፅንፈኛ ቡድኖች እንዳሉ እናምናለን፡፡ በአካባቢው የዕምነት መቻቻል እንዳይኖር የሚሰብኩ እንደ ኽዋሪጃ ዓይነት ቡድኖች መኖራቸውን እናውቃለን፡፡" ብለዋል፡፡

የእሥልምና አክራሪ የሆኑና የሽብር ቡድኖች በአካባቢው የመስፋፋታቸውን ጉዳይ መንግሥታቸው በቅርብ እየተከታተለ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡

በየመን በፖሊስና በተቃዋሚ ሰልፈኞች መካከል በተካሄደው ደም አፋሣሽ ግጭት ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት መግለጫ የየመን መረበሽና መውደቅ ወይም እንደመንግሥት መጨናገፍ ቢከተል ለመላው የአፍሪካ ቀንድ አደገኛ የፀጥታ ችግር እንደሚተርፍ ያስጠነቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ "የየመን የተቃውሞ ሰልፎች ወደ ሕግ መጣስ እና ሥርዓት አልበኝነት ካመሩ መሠረቱን በዚያ ላደረገው አልቃይዳ ለመስፋፋት መልካም ዕድል ይፈጥርለታል፡፡" ብለው አሁንም ባለው ሁኔታ ለአልሻባብ መልካም የድጋፍ መሠረት እንደሆነለት ተናግረዋል፡፡

የአልቃይዳ ግብረ አበር በሆነው በአልሻባብ ላይ የሶማሊያ መንግሥት እና የአፍሪካ ሕብረት የከፈቱትን ዘመቻ ለመቀላቀል ጦራቸውን ወደዚያ ያዘምቱ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስሩ ተጠይቀው ነበር፡፡

ያንን እንደማያደርጉ ተናግረው ይሁን እንጂ በሶሚሊያ የድንበሩ ወገን የኢትዮጵያ ወታደሮች በግጭቶች ውስጥ የመግባታቸውን ነገር ግን አልካዱም፡፡

"አንዳንድ ጊዜ ካለህበት ሥፍራ ጥቂት አሥር ሜትሮች ርቀት ላይ ከባድ ፍልሚያ እየተካሄደና ከፊት ለፊትህ የተቀመጠው ጠላትህ ሆኖ እያለ በእንደዚህ ዓይነት ውጊያ ውስጥ አለመቀላቀል ወይም በውጊያው አለመወሰድ በጣም ይከብዳል፡፡" ብለዋል፡፡

ባለፉ ጥቂት ሣምንታት ውስጥ የሶማሊያ ወታደሮችና የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ (አሚሶም) ኃይሎች በአልሻባብ ተዋጊዎች ላይ የከበዱ ጉዳቶችን አድርሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሰላም አስከባሪዎቹ ላይ ደረሰ የተባለው ሃምሣ አባላቱን በውጊያዎቹ ውስጥ ማጣት የማጥቃቱን እርምጃ እንዳቀዘቀዘው አቶ መለስ ጠቁመዋል፡፡

"አሚሶም ወታደራዊ ግፊቱ የቀዘቀዘ ይመስለኛል፡፡" - የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ - ይሁን እንጂ ከውጊያ ውጭ የሆነ ወይም ብቃቱ የሌለው ኃይል ነው ብለው እንደማያምኑ ገልፀዋል፡፡

ስትራተጂክ በሆነችው ጅቡቲ በሚቀጥለው ወር ይደረጋል ከተባለው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በፊት በከተማይቱ ውስጥ ፍንዳታዎች ሊደርሱ እንደሚችሉ የተነበዩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሃገሪቱ ውስጥ ያሉ ፅንፈኛ ቡድኖችን በፈንጂዎቹ በማስታጠቅ አለመረጋጋትን እያቦካ ነው ሲሉ በአካባቢው ዋነኛውን ባላንጣቸውን የኤርትራን መንግሥት ወንጅለዋል፡፡

ሰሞኑን ጅቡቲ ውስጥ ተቃዋሚ ኃይሎች ሰልፎችን አካሂደው እንደነበረና እንቅስቃሴዎችም እንዳሉ የተነሣላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሁኔታው እንደ የመንና እንደ ግብፅ ሊሆን ይችላል የሚል የተለየ ሥጋት እንደማያሣድርባቸው ተናግረዋል፡፡

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG