በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትግራይ 400 የጾታ ጥቃት ተጎጂዎችን በግላቸው የረዱት የሕክምና ባለሞያ ተሸለሙ


ሲስተር ካሕሳ ሐጎስ
ሲስተር ካሕሳ ሐጎስ

የካናዳው “ዓለም አቀፍ የሴቶች ሰላም እና ጸጥታ ድርጅት”፣ በትግራይ ክልል በሴቶች ጥቃት ላይ ሲሠሩ ለነበሩ የሕክምና ባለሞያ ሽልማት ሰጠ።

በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ በተስፋፋው ጦርነት ወቅት፣ በክልሉ ውስጥ የጾታ ጥቃት የተፈጸመባቸውን 400 የሚደርሱ ሴቶችን፣ በራሳቸው ጥረት እና ወጪ ያገለገሉት ሲስተር ካሕሳ ሐጎስ ተመርጠው መሸለማቸውን፣ የካናዳ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር አሕመድ ሑሴን ገልጸዋል።

የዓዲ ግራት ሆስፒታል ሠራተኛዋ ሲስተር ካሕሳ፣ ሽልማቱን ከተቀበሉ በኋላ ባሰሙት ንግግር፥ ሽልማቱን፣ በትግራይ ክልል የጾታ ጥቃት በተፈጸመባቸው ሴቶች እና እነርሱን በረዱ የጤና ባለሞያዎች ስም እንደተቀበሉ ገልጸዋል።

የካናዳ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር አሕመድ ሑሴን በበኩላቸው፣ በጦርነቱ ወቅት በትግራይ ክልል፣ “በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን፣ እንዲሁም በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሴቶች የጾታ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው” አስታውሰዋል።

በክልሉ የካናዳ መንግሥት የሚደጉማቸው ሰባት የሕክምና ማዕከላት በሥራ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በተባበሩት መንግሥታት በኩል ደግሞ ጾታዊ ጥቃት ለተፈጸመባቸው ሴቶች 65 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን ጠቅሰዋል።

ተዋጊ የነበሩ የሠራዊት አባላትን ወደ ማኅበረሰቡ ለማዋሐድ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ፣ ካናዳ፣ 14 ሚሊዮን ዶላር መለገስዋን ሚኒስትሩ አንሥተዋል።

ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ጋራ የተነጋገሩት የካናዳ ዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ሚኒስትሩ አሕመድ ሑሴን፣ የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበር ካናዳ ድጋፍዋን እንደምትቀጥል ማረጋገጣቸውን፣ ዘጋቢያችን ሙሉጌታ አጽብሓ ከመቐለ አድርሶናል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG