በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን ላይ አዲስ ማዕቀብ በመጣል ብሪታንያን እና የአውሮፓ ሕብረትን ተቀላቀለች


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ

የኢራን መንግሥት በተቃዋዎች ላይ እየወሰደ ባለው እርምጃ ሳቢያ የአውሮፓ ህብረት እና ብሪታንያ እንዳደረጉት ዩናይትድ ስቴትስም በተመሳሳይ ትላንት ሰኞ ኢራን ላይ አዲስ ማዕቀብ ጥላለች።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ አዲሱ ማዕቀብ የኢራኑን ምክትል የደህንነት ሚኒስትር እና የአብዮታዊ ዘቡን ዋና ዋና አዛዦች ጨምሮ 10 ሰዎችን ያካተተ ነው።

“ማዕቀቡ የኢራንን መንግሥት የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ተጠያቂነት እውን ለማድረግ የታለመ ነው” ያሉት ፕራይስ አክለውም "የዛሬው እርምጃ ከአጋሮቻችን ጋር በቅርበት በመመካከር የደረስንበት፣ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ጭካኔ የተሞላበት የኃይል እርምጃ ከሚፈጽሙት የኢራን ባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት ባላቸው ግለሰቦች እና አካላት ላይ ከተነጣጠሩት በርካታ ማዕቀቦች ውስጥ የቅርቡ ነው” ብለዋል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ የአውሮፓ ህብረት እና ብሪታንያ አዲስ የጣሏቸውን ማዕቀቦች አውግዞ የአጻፋ እርምጃ እንወስዳለን ብሏል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ በሰጡት በዚህ መግለጫ "እስላማዊቱ ሪፐብሊክ በአውሮፓ ህብረት እና በእንግሊዝ የሰብአዊ መብት ደፍጣጮች ላይ በቅርቡ የምትወስዳቸውን አዳዲስ ማዕቀቦች ዝርዝር ይፋ ታደርጋለች" ብለዋል።

የአውሮፓ ህብረት ትናንት ሰኞ ይፋ ያደረገው ማዕቀብ በበርካታ የኢራን ባለሥልጣናት እና ድርጅቶች ላይ የተነጣጠረ ነው። ዝርዝሩም የኢራኑን የስፖርት እና የወጣቶች ሚኒስትር ሃሚድ ሳጃዲን፣ የኢራኑን ልዩ የፖሊስ ኃይል፣ የአብዮታዊ ዘቡን ከፍተኛ መኮንኖች እና በርካታ የሳይበር ደህንነት ኃላፊዎችን፣ እንዲሁም የኮምፒውተር ጠለፋ ለማድረግ የሚውሉ የተለያዩ የኢንተርኔት ፕሮግራሞች እና የደህንነት መሳሪያ ኩባንያዎችን ያካተተ ነው።

የብሪታንያው ማዕቀብ በአንጻሩ የኢራኑን ምክትል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አህማድ ፋዜሊያን ይጨምራል። የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ፋዜሊያን ‘የሞት ቅጣትን ለፖለቲካ ፍጆታ ያዋለ እና ኢፍትሃዊ’ ባለው የሃገሪቱ የፍትህ ርዓት ተጠያቂ አድርጓቸዋል።

ይህንኑ አስመልክቶም የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀምስ ክሌቨርሊ በሰጡት መግለጫ “ዛሬ ማዕቀብ የተጣለባቸው የሞት ቅጣትን ለፖለቲካዊ ዓላማዎች ማሳኪያ ከሚጠቀሙት ከፍትህ አካላት፣ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰልፈኞችን እስከሚደበድቡት ወረበሎች ድረስ፣ አገዛዙ በኢራን ሕዝብ ላይ የሚፈጽመው ጭካኔ የተሞላበት በደል ተዋናዮች ናቸው።” ሲሉም ወንጅለዋል።

XS
SM
MD
LG