በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሳውዲ ልዑል አልጋ ወራሽ የአካባቢው ሀገሮች ጉብኝት


የቱርክ ፕሬዚደንት ታዪፕ ኤርዶዋን፣ የሳውዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን
የቱርክ ፕሬዚደንት ታዪፕ ኤርዶዋን፣ የሳውዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን

ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ግብጽን የጎበኙት የሳውዲ አረቢያ አልጋ ወራሽ ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ትናንት ረቡዕ ደግሞ ዮርዳኖስን እና ቱርክን ጎብኝተዋል። ልዑሉ ጉብኝቱን ያደረጉት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በሚቀጥለው ወር በሳውዲ አረቢያ ከሚያደርጉት ጉብኝት አስቀድሞ ነው። በፕሬዚደንቱ ጉብኝት ወቅት የነዳጅ አቅርቦትን ጨምሮ በርካታ አካባቢውን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚካሄድ ኤድዋርድ ዪሬንያን ከካይሮ ለቪኦኤ ያጠናቀረው ዘገባ አመልክቷል።

የሳውዲው ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን ትናንት በጎበኟቸው በዮርዳኖስ እና በቱርክ ማክሰኞ ዕለትም በግብፅ እንደርዕሰ ብኄር አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በካይሮ ጉብኝታቸው ከከፍተኛ ግብፅ መሪዎች ጋር የተነጋገሩት ሳልማን በሰባት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ወጪ አስራ አራት የተለያዩ የንግድ ሥምምነቶችን ፈርመዋል። ሳውዲ በዮርዳኖስም ግዙፍ መዋዕለ ነዋይ የመደበች ሀገር እንድመሆኗ የአልጋ ወራሹ ጉብኝት በዚያ ረገድ ያላትን ስፍራ አጠናክሮላታል።

የሳውዲው አልጋ ወራሽ የክልሉን ሀገሮች እንደሚጎበኙ ሲጠበቅ የቆየ ቢሆንም አሁን መደረጉ የሰማኒያ ስድስት ዓመቱ አባታቸው ንጉሥ ሳልማን ቢን አብዱልአዚዝ ጤና እያጡ በመሄዳቸው ምክንያት ሳይሆን አይቀርም።

በቱርክ እና በዮርዳኖስ ያደረጉት ጉብኝት በሪያድ እና በሁለቱ በመካከለኛው ምስራቅ ቁልፍ ቦታ ባላቸው ሀገሮች መካከል ያለውን የንግድ እና የፖለቲካ ግንኙነት ያንጸባርቃል።

በሳውዲው አልጋ ወራሽ ጉብኝት የኢራን ጉዳይ፥ የየመን ሁኔታ እና የክልላዊ መከላከያ ጉዳዮች ላይ ውይይት መደረጉን ተንታኞች ገልጸዋል። የሳውዲው ልዑል የኢራቅ ጉብኝት ግን የፖለቲካዋ ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ እና አዲስ መንግሥት ለማቋቋም ባለመቻሏ ተላልፏል።

ግብጻዊው የፖለቲካ እና የማህበራዊ ጉዳዮች ተንታኝ ሳዪድ ሳዲክ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ዝግጅት ሲደረግበት የቆየው የልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን የአካባቢው ሀገሮች ጉብኝት የተደረገው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በሚቀጥለው ወር ከሚያደርጉት ጉብኝት አስቀድሞ እና የኢራን የኒውኪየር አቅም ያሳደረው ስጋት እየጨመረ ባለበት ባሁ ወቅል መሆኑን አንስተዋል።

"መሐመድ ቢን ሳልማን ኢራንን በአየር መከላከያ መክበብ ይፈልጋሉ።ስድስት የሰላጤው ሀገሮች፥ ዮርዳኖስ ግብጽ እና እስራኤል የሚሳተፉበት ወታደራዊ አማራጭ ሊኖረን ይችላል በማለት ኢራን የበረታ ጫና ማድረግ ይፈልጋሉ። ፕሬዚደንት ባይደን ጉብኝት ስለሚያካሂዱም የክልሉ ሀገሮች መሪዎች በብዛት በየሀገሩ የሚሄዱትም ከዚያ አኳያ ምን ዐይነት አቋም እንዳለ ለመመልከት ነው።" ብለዋል።

ሪያድ ከእስራኤል ጋር በግልጽ ሳይሆን ግንኙነቷን ታጠናክራለች ተብሎ እንደሚጠበቅ ተንታኙ አክለው የአየር መከላከያ ስትራተጂውም የዚሁ አካል እንደሆነ ገልጸዋል። በይፋ የሚደረግ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ልውውጥ ግን የሚኖር አይመስልም ብለዋል።

ግብፅም በዚህ የአየር መከላከያ ስትራተጂ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ሊሆን ይችላል እንጂ ለመሳተፍ ዳር ዳር እያለች እንደሆነ ተንታኙ ይናገራሉ። የሰላጤው ሀገሮች አሉ አስከትለው ከፕሬዚደንት ባይደን ጉብኝት በኋላ የሰላጤው ሀገሮች ለዩናይትድ ስቴትስ የሚሸጡትን ነዳጅ መጠን ከፍ ማድረጋቸው አይቀርም።

በፓሪስ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ኻተር አቡ ዲያብ በበኩላቸው ለቪኦኤ በሰጡት ቃል መሐመድ ቢን ሳልማን በአካባቢው ሀገሮች ያደረጉት ጉብኝት የአልጋ ወራሽነት ጉዞአቸው አንድ ምዕራፍ መሆኑን እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ ያለው የአረብ ሀገሮች ህብረት ግንባር ቀደም መሪ ሆነው ለመገኘት እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

አረብ ሀገሮች ኢራን እና ፍልስጥኤምን እንዲሁም ዩናይትድ ስቴትስን በሚመለከቱ ዋና ዋና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም እንዲኖራቸው ያስፈልጋል ያስፈልጋል ያሉት ተንታኙ በሩስያ እና በዩክሬይን መካከል የቀጠለው ጦርነት በአረብ ሀገሮች እና በዩናይትድ ስቴትስ ግንኙነት ላይ ተጨማሪ ችግር እያስከተለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የሳውዲው ልዑል ቱርክን ከመጎብኘታቸው አስቀድሞ የቱርክ ፕሬዚደንት ታዪፕ ኤርዶዋን በቅርቡ ሪያድን ጎብኝተው እንደነበር ተንታኙ ኻተር አቡ ዲያብ አስታውሰዋል።

የኤርዶዋን ጉብኝት አንካራ ከሳውዲያዊ ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጊ መገደል ተከትሎ ከሪያድ ጋር ስታደርገው የነበረውን እሰጥ አገባ እንዳቆመች እና አሁን አመዛኙ ትኩረቷ ከሳውዲ አረቢያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ግንኙነት ማሻሻል መሆኑን እንደሚጠቁም አመልክተዋል።

XS
SM
MD
LG