በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን የህዝብ ውሳኔ ተቀባይነት ካላገኘ የአካባቢ አለመረጋጋት ሊፈጥር ይችላል ተባለ


ታቦ ምቤኪ
ታቦ ምቤኪ

በመጭው አመት የሚካሄደው የደቡብ ሱዳን ህዝበ ውሳኔ ተቀባይነት ባለው መልኩ ካልተካሄደ በአካባቢው አለመረጋጋትን ሊፈጥር እንደሚችል የአፍሪካ ህብረት የሱዳን ከፍተኛ ልኡክ ታቦ ምቤኪ ተናገሩ።

ባለፈው ሳምንት ከዩናይትድ ስቴይትሱ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተን ጋር በዋሽንግተን በተለይ በሱዳን ጉዳይ የተነጋገሩት ፕሬዝደንት ምቤኪ የሱዳንን የፖለቲካ ሁኔታ አስመልክቶ የሚታየው አለም አቀፍ ድጋፍ እንዳበረታታቸው ይናገራሉ።

የዩናይትድ ስቴይትስ መንግስትና ህዝብ የደቡብ ሱዳን የህዝብ ውሳኔ በቀነ-ቀጠሮው እንዲካሄድ የገንዘብ፣ የፖለቲካና የሰው ሀይል እገዛ በሰፊው መኖሩንና ይሄም ተጠናክሮ አንዲቀጥል ሚስተር ምቤኪ ለፕሬዝደንት ኦባማ አሳስበዋል።

በደቡብ አፍሪካ በመካሄድ ላይ ባለው የአለም ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ ላይ የነበሩት ምክትል ፕሬዝደንት ጆ ባይደንንም አግኘተው በሱዳን ጉዳይ እንዳወያዩአቸውም ሚስተር ምቤኪ ተናግረዋል።

ለአስርት አመታት የዘለቀው የሰሜን-ደቡብ ሱዳን ውጊያ በ1998 በተፈረመው የCPA ስምምነት ሲፈታ በስምምነቱ ከተካተቱት መስፈርቶች አንዱ የውሳኔ ህዝብ እንደነበር ይታወቃል።

በደቡብ ሱዳን ህዝብ ውሳኔ የአፍሪካ ህብረት አባላት የማያሻም ስምምነት አላቸው ያሉት ታቦ ምቤኪ፣የአፍሪካ ህብረት የሱዳንን ውሳኔ ህዝብ እንደሚደግፍና ሱዳንን የሚያዋስንኑት 9 አገሮች በተለይ በቅርበት የጋር መፍትሄ ለማበጀት መስራት እንዳለባቸው አክለው ጨምረዋል። ከነዚህ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ እንዳለችበትም ሚስተር ምቤኪ ይናገራሉ።

“የኢጋድ ተረኛ ሊቀ-መንበርነቱ በኢትዮጵያ እጅ ስለሚገኝ፤ በሰፊው በዚህ ሂደት ይሳተፋሉ” ሲሉ የተናገሩት ምቤኪ ሰኔ 14 ቀን በአዲስ አበባ በቅድመ-ሬፈረንደምና ከዚያ በኋላ በሚነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ለመነጋገር ስብሰባ ጠርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም በሱዳን ፖለቲካ ዙሪያ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ሚስተር ምቤኪ ተናግረዋል። “ውጤቱ ምንም ይሁን ምን፤ ወደ ውጥረትና ግጭት ሊያመራ አይገባውም። ትንሽም ይሁን ትልቅ የሆነ መተናኮስ ወይንም ጦርነት ተቀባይነት የሌላቸው አካሄዶች ናቸው፣” ብለዋል።

አንዳንድ ተንታኞች የሱዳን የህዝበ-ውሳኔ ፍጹም ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻና የህዝቡን ድምጽ በሚያስከብር መልኩ ካልተካሄደ ግጭቱ ለጎረቤት አገሮችም የራስ ምታት ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። ያ’ እንዳይሆን የጎረቤት አገሮች፣ የአፍሪካ ህብረትና የአለም-አቀፉ ማህበረሰብ ከሱዳን የፖለቲካ ሀይሎች ጋር አብረው እየሰሩ እንደሆነ የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ የሱዳን ልኡክ ታቦ ምቤኪ ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG