በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በምያንማር ሁለት ሰላማዊ ሰልፈኞች በተገደሉ ማግስት ዛሬም ብዙ ሺዎች ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተዋል


Myanmar soldiers stand guard
Myanmar soldiers stand guard

በምያንማር ፖሊስ ሁለት ሰላማዊ ሰልፈኞች በገደለ ማግስት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ዛሬ ባለፈው ጥር 24, 2013ዓም የተፈጸመውን ወታደራዊ የመንግስት ግልበጣ በመቃወም አደባባይ ወጥተዋል።

የሰዎች ህይወት የጠፋበትን የኃይልም እርምጃ ያወገዙት የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬሽ ትላንት ማምሻው ላይ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ“በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ህይወት አጥፊ ኃይል መጠቀም፣ ማስፈራራት እና ትንኮሳ መፈጸም ተቀባይነት የለውም” ሲሉ ገልጠዋል።

በምያንማር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ መልዕክተኛ ቶም አንድሩ በበኩላቸው በተመሳሳይ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ “ማንዳላይ ላይ የተገደለውን አንድ ታዳጊ ጨምሮ ገዥው ወታደራዊ ሁንታ በምያንማር እያደር እያጠናከረ በመጣው የጭካኔ ድርጊቱ የሰዎች ሕይወት የሚጠፋበት ሁናቴ አሳስቦኛል፡፡ ከሰልፍ መበተኛ የውሃ መድፍ እስከ የጎማ ጥይቶች እና አስለቃሽ ጭስ፤ አሁን ደግሞ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ጥይት የሚነጣጠርበት ይህ እብደት ማብቃት አለበት!” ብለዋል።

በቅዳሜው ሰልፍ ወቅት ሃያ ሰዎች መቁሰላቸውን እና 569 ሰዎች ደግሞ መታሰራቸውን አንድ የድንገተኛ ጊዜ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊዎች ተጠሪ አመልከተዋል።

በትላንትናው ዕለት ያንጉን ላይ በተካሄደ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተሳተፈ እና “ሲቪሎችን ለተቃውሞ አነሳሳተሃል” በሚል የተወነጀለ ሉ ሚን የተባለ አንድ ታዋቂ ተዋናይ ዛሬ ማለዳ ላይ መታሰሩ ተገለጠ። ሉ ሚን በተከሰበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የሁለት ዓመት እስራት ፍርድ ሊገጥመው ይችላል። ፖሊስ አክሎ እንደገለጠው ሉ ሚን በጸረ-ብጥብጥ ወንጀል ተጠያቂ ለማድረግ ከሚፈልጋቸው ስድስት ታዋቂ ሰዎች አንዱ ነው ብሏል።

በሉ ሚን የፌስቡክ ገጽ ላይ በተለጠፈ ቪዲዮ መልዕክት ፖሊሶች ያንጉን ወደሚገኘው ቤታቸው መጥተው ይዘውት መሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡

"በሩን በኃይል ከፍተው በመግባት ይዘውት ወጡ። ወደ የት እንደሚወሰዱ ግን አልነገሩኝም፡፡ ማቆምም አልቻልኩም።" ሲሉ የተዋናዩ ባለቤት ክሂን ሳባይ ኦ ተናግረዋል፡፡

XS
SM
MD
LG