በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በማይፀምሪ በተካሔደ ሰልፍ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እንዲከበር ተጠየቀ


በማይፀምሪ በተካሔደ ሰልፍ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እንዲከበር ተጠየቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:48 0:00

በማይፀምሪ በተካሔደ ሰልፍ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እንዲከበር ተጠየቀ

የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እንዲከበር የሚጠይቅ ሰልፍ፣ በምዕራብ ጠለምት ወረዳ እና ማይፀምሪ ከተማ መካሔዱን፣ የአሜሪካ ድምፅ በስልክ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከትግራይ ክልል በኩል ተሰንዝሯል ያሉት ጥቃት እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል።

የፌደራሉ መንግሥት “አከራካሪ” ከሚላቸው የትግራይ እና የአማራ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ ከሚያነሡባቸው አካባቢዎች አንዱ በኾነው የምእራብ ጠለምት አካባቢ፣ ትላንት ሰላማዊ ሰልፍ መካሔዱን፣ መምህር ኣብርሃ ተሾመ የተባሉ የምእራብ ጠለምት ነዋሪ በስልክ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡

ለደኅንነታቸው ስለሚሰጉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሌላው የማይፀምሪ ከተማ ነዋሪ፣ በቀደመው ጦርነት ከደረሰው ጉዳት ትምህርት በመወሰድ፣ ችግሮች በሰላም እንዲፈቱና ተጨማሪ ግጭት ሊኖር እንደማይገባ አመልክተዋል።

ለ30 ዓመታት የማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን ሲያነሡ መቆየታቸውን ያወሱት መምህር አብርሃም የተባሉት አስተያየት ሰጪ፣ ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል፣ ሰልፉ በግዳጅ የተካሔደ ስለመኾኑ፣ በማይፀምሪ ከተማ የሚኖሩና ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የትግራይ ክልል ተወላጅ ተናግረዋል። በሰልፉ ላይ በግዳጅ እንደተሳተፉ የጠቀሱት ነዋሪው፣ የአካባቢው ሕዝብም በግዳጅ ገንዘብ እንዲያዋጣ መደረጉን፣ መቀሌ ለሚገኘው ዘጋቢያችን ሙሉጌታ አጽብሓ ነግረውታል።

የማይፀምሪ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ አቶ ሙሉዓለም ሹመት ግን፣ በእኚኹ ነዋሪ የቀረበውን ክስ “ሐሰት” ሲሉ አጣጥለውታል፡፡

ከማይፀምሪ ተፈናቅለው በእንዳባጉና ወረዳ የሚገኙት አቶ ባራኺ ዓለምሸት የተባሉ ተፈናቃይ በበኩላቸው፣ በማይፀምሪ እና አካባቢዋ “ወራሪ” ሲሉ በጠሯቸው ኀይሎች ሕዝቡ እየተንገላታና እየተፈናቀለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ትላንት በተካሔደው ሰልፍ ሕዝቡ “ተገዶ የወጣ ነው” ያሉት አቶ ባራኺ፣ አካባቢው ከስሙ ጀምሮ ትግርኛ መኾኑን ገልጾ፣ “ሕዝቡም መሬቱም ትግራይ ነው፤” በማለት ሞግቷል።

በተመሳሳይ በራያ አላማጣ ወረዳ እና ኮረም ከተማ አካባቢዎች፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ታጣቂዎች፣ ወታደራዊ ትንኮሳ ከመፈጸም ባለፈ የተወሰኑ አካባቢዎችን በመቆጣጠር ለሰዎች ሞት፣ ለንብረት ውድመት ምክንያት ኾነዋል፤ ሲሉ ክስ ማሰማታቸው ይታወሳል።

ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየታቸውን የሰጡት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ ረዳኢ ኃለፎም ግን፣ ውንጀላውን አስተባብለው በአንጻሩ ትንኮሳው፣ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ላይ ነው የተፈጸመው ብለዋል፡፡ አካባቢዎቹ የትግራይ ክልል ይዞታ ኾነው ሳለ “ወረራ ተፈጸመብን” የሚል ክስም ትርጉም አይሰጥም ማለታቸው አይዘነጋም።

የማንንት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በሚነሣባቸው እንዲሁም የፌደራሉ መንግሥት አወዛጋቢ በሚላቸው የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ተከትሎ፣ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶክተር ለገሰ ቱሉ ባለፈው ሳምንት በሰጡት መግለጫ፣ ከሰሞኑ በትግራይ ክልል በኩል በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታየው አዝማሚያ፣ የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት የሚጥስ ነው፤ ብለው ነበር፡፡

የሚነሡ ጥያቄዎችንና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት እና በድርድር ከመፍታት ይልቅ፣ ወሰንን በኀይል እናስከብራለን፤ የሚል አካሔድ፣ “ካለፈው ስሕተት አለመማርን ያመለክታል፤ ሰላሙን እያጸና የሚገኘውን የትግራይ ሕዝብም ለሌላ ዙር ሥቃይ እና እንግልት ይዳርጋል፤” ሲሉም መናገራቸው ይታወሳል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የሚነሡት የማንነት ጥያቄዎች አግባብነት የላቸውም፤ ሲል ጥያቄውን ያጣጥለዋል፡፡ ጥያቄዎች፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ቀድሞ መቅረብ ያለባቸው ለክልሉ መንግሥት ነው፤ በማለትም አካሔዱን ይቃወማል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ጥያቄ አቅራቢዎቹ፣ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርገን ላቀረብነው ጥያቄ፣ የክልሉ መንግሥት ምላሽ ባለመስጠቱ፣ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት፣ ጉዳያችን በሕዝበ ውሳኔ እንዲፈታ ለፌዴሬሽን ም/ቤት ማቅረባቸውን አስረድተዋል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG