ዋሺንግተን ዲሲ —
ማይካድራ ላይ በተካሄደው ጭፍጨፋ የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦችና ተባባሪ ናቸው የተባሉ ሌሎች ሦስት ሰዎች ዛሬ በፌደራል መካከለኛ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት መቅረባቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ምርመራውን የያዘው ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ሲያሰባስብ መቆየቱን ለፍርድ ቤቱ ማሳወቁንና ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ጭፍጨፋው እንዲፈጸም ካደረጉ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ሸሽተው በተባባሪነት የተያዙት ሦስት ሰዎች ቤት ውስጥ መሸሸጋቸውን ማስረዳቱን ዘገባው ጠቁሟል።
ፖሊስ ከተጠርጣሪዎቹ መኖሪያ ቤቶች ማስረጃዎችን ማሰባሰቡንና ለቴክኒክ ምርመራ ወደሚመለከተው አካል መላኩን ገልፆ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መጠየቁን የዜና አገልግሎቱ ዘግቧል።
ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና መብት እንዲከበርላቸውና ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጎ ለፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ኢዜአ አክሎ ዘግቧል።