በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሜይ ዴይ የሠራተኞች ቀን - ሜይ ዴይ የፀደይ በዓል


ዛሬ ሜይ ዴይ ነው - ሚያዝያ 23 /በአውሮፓ ደግሞ ሜይ አንድ/ ዓለምአቀፍ የሠራተኞች፣ የወዝአደሮች ወይም የላብአደሮች ቀን በዓለም ዙሪያ ይከበራል፡፡

ዛሬ ሜይ ዴይ ነው - ሚያዝያ 23 /በአውሮፓ ደግሞ ሜይ አንድ/ ዓለምአቀፍ የሠራተኞች፣ የወዝአደሮች ወይም የላብአደሮች ቀን በዓለም ዙሪያ ይከበራል፡፡ የዛሬው ሜይ ዴይ በብዙ ሃገሮች ውስጥ በሰላማዊ ሰልፎችና በቅስቀሳ ዘመቻዎች የተሞላ ነበር፡፡ ፈረንሣይና ቱርክ ውስጥ እስከ ትርምስና ግጭት የደረሱ ሁኔታዎች ተከስተዋል፡፡

ወትሮም በደም ለታጀበ ሜይ ዴይ አዲስ ያልሆነው የቱርክ ዋና ከተማ ኢስታንቡል ዛሬም በታክሲም አደባባይ ፖሊስ ሰልፈኞችን ለመበተን አስለቃሽ ጋዝ ረጭቷል፡፡ ሁለት መቶ ሰው ታስሯል፡፡

በተለይ ራቸፕ ታዪፕ ኤርዶዋን ፈላጭ ቆራጭ የሚያደርጋቸውን ሥልጣን የሚሰጥ የሕገመንግሥት ማሻሻያ ውሣኔ ሕዝብ በጠባብ ልዩነት ካሸነፉ ወዲህ ቱርክ ውስጥ የሚታየው የተቃውሞ ውጥረት እያየለ መጥቷል፡፡

ሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ ውስጥ ደግሞ እጅግ የተዋበ በተባለው የዛሬው የፀደይ ዕለት መቶ ሺህ የሚሆን ሰው አደባባይ ውሎ ጎዳናውን ያደመቀው መሆኑ ተዘግቧል፡፡

«ይህንን ያህል ሰው ሲሰባሰብ ኅብረት መኖሩን ያሳያል፡፡ ይህ የሥራና የሰላም ቀን ነው፤ የአየሩም ሁኔታ ውብ ነው፡፡ የሰዉን የደስታ ስሜት ደግሞ ፊቱ ላይ ማንበብ ይቻላል» ብሏል ሞስኮ ላይ ሰልፍ የወጣው ዩሪ ለቪኦኤ ሲናገር፡፡

ፈረንሣይ ደግሞ አሁንም የምትገኘው በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ ከአንድ ሣምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ውጥረት የበዛበትን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ስለምታካሂድ ሥጋቱ የበረታ ነው፡፡ መንግሥቱ የሚገኘው በሙሉ የተጠንቀቅ ሁኔታ ላይ ነው፡፡

ከፓሪስ ወጣ ብለው ቅስቀሳ ሲያደርጉ የዋሉትን ወደ ግራም ወደ ቀኝም ያላዘመሙ ናቸው የሚባሉትን የዕጩ ኢማኒኤል ማክሮን እና የሙስሊሞችን ወደ ሃገራቸው መፍለስ እንደሚያስቆሙና ሃገራቸውን ከአውሮፓ ኅብረት ለማስወጣት እየዛቱ ያሉትን የብሄረተኛዪቱን ዕጩ ማሪን ሎ ፔንን ደጋፊዎች በየጎራቸው ከፋፍሎ ለመጠበቅና ግጭትን ለማስወገድ ፓሪስ ላይ ዘጠኝ ሺህ ፖሊሶች ተሰማርተዋል፡፡

ፓሪስ እምብርት ላይ ደግሞ በሺኾች የሚቆጠሩ በተለይ ማሪን ሎ ፔንን የሚቃወሙ ሰልፈኞች ጎዳናዎቹን አጣብበው ውለዋል፡፡

የሠራተኞች ማኅበር መሪው ዦን ክሎድ ማይሊ «ማሪን ሎ ፔንን ማቆም አለብን፡፡ በዚህ ሁላችንም እንስማማለን፡፡ ተጨማሪ ድምፅ እንዳያገኙና ተቀባይነታቸውም ከፍ እንዳይል ማድረግ አለብን፡፡ ማሪን ሎ ፔን ብዙ መዘዝ የሚያመጡብን ሰው ናቸው» ብለዋል፡፡

ማኒላ ላይ የፊሊፒንስ የሠራተኞች መብቶች ተሟጋች ቡድኖችና የሠራተኛ ማኅበራት፤ ጃካርታ ላይ ደግሞ በሺኾች የሚቆጠሩ ሠራተኞች የመብቶች ጥያቄዎችን እያነገቡ ወደ ጎዳና ወጥተው ውለዋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ደግሞ ሜይ ዴይ ወደ ፍልሰት ቀን የተቀየረ ይመስላል፡፡

ከኒው ዮርክ እስከ ሎስ አንጀለስ ባሉ ከተሞች ውስጥ የዶናልድ ትረምፕን እየጨመረ የመጣ ፍልሰተኞችን በኃይል የማስወጣት ውሣኔና አድራጎት የሚቃወሙ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እየተሰለፉ ነው፡፡

በአንዳንድ ከተሞች ደግሞ አሜሪካ ያለ ፍልሰተኞች ምን እንደምትመስል ለማሣየት በሚል ፍልሰተኛ ሠራተኞች ዛሬን የሥራ ማቆም አድማ መትተው እንዲውሉ የተቃዋሞዎቹ አስተባባሪዎች ጠይቀዋል፡፡

በነገራችን ላይ ሜይ ዴይ በዓለማችን ሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ባሉ ማኅበረሰቦሰች ዘንድ የሚከበር የፀደዩ ወቅት ጥንታዊ፣ ደማቅ እና ዓመታዊ ክብረ በዓል ነው፡፡

የሜይ ዴይ ባሕላዊ በዓል አከባበር በእንግሊዝ ሰሴክስ ቢሾፕስቶን ቤተክርስትያን፤ ሚያዝያ 23/2009 ዓ.ም.የፎቶ ምንጭ፤ ዊኪፔድያ
የሜይ ዴይ ባሕላዊ በዓል አከባበር በእንግሊዝ ሰሴክስ ቢሾፕስቶን ቤተክርስትያን፤ ሚያዝያ 23/2009 ዓ.ም.የፎቶ ምንጭ፤ ዊኪፔድያ

ሜይ ዴይ የሠራተኞች ቀን የሆነው በሃያ ሃገሮች ውስጥ በሚገኙ ሶሾሊስቶችና የሠራተኞች መብቶች ተሟጋች ፓርቲዎች (በኢት.የዘ.አቆ) ሚያዝያ 23 / 1881 ዓ.ም ፓሪስ ላይ የተመሠረተውና እስከ 1908 ዓ.ም የዘለቀው የሁለተኛው ሶሻሊስት ዓለምአቀፍ ጉባዔ ከወሰነ በኋላ ነው፡፡

ማክሰኞ፤ ሚያዝያ 26 / 1878 ዓ.ም ቺካጎ ከተማ ውስጥ ሄይማርኬት አደባባይ ላይ መብቶቻቸውን ለመጠየቅ ሰልፍ በወጡ ሠራተኞች ላይ ቦምብ ተጥሎ ብዙ ደም ፈሰሰ፤ ይህ ዕለት በየዓመቱ ተዘክሮ እንዲውል ነበር ሁለተኛው ሶሻሊስት ኢንተርናሽናል በፓሪሱ ጉባዔ ላይ የወሰነው፡፡ እነሆም አጋጣሚ ሆነና የፌሽታና የፈንጠዝያው ሜይ ዴይ በዚህ ሁኔታ ከኀዘንና ከዝክሩ ሜይ ጋር ገጠመ፡፡ ጊዜ እየረዘመ ሲመጣም የኋለኛው ሜይ ዴይ የፊተኛውን ዋጠውና ስለሜይ ዴይ ሲወራ ፈጥኖ የሚታወሰው የሠራተኛው ቀን ሜይ ዴይ ሆነ፡፡ የጥንቱ የጠዋቱ፤ ባሕሉ ሳይሆን አዲሱ ሜይ ዴይ እነሆ ዛሬ ልክ 128ኛው ሆነ፡፡

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG