ቱርክ ሰሜን ሶሪያ ውስጥ በሚንቀሳቀሱት በዩናይትድ ስቴትስ ደጋፊ ሚሊሽያዎች ላይ ያደረሰችው ጥቃት ትኩረቱን ከፀረ እሥላማዊ መንግሥት ተዋጊዎች ላይ የሚነጥቅ አድራጎት ነው ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስትር ጂም ማቲስ አጥብቀው አወገዙ።
ጂም ማቲስ ኢንዶኔዥያ ውስጥ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል አፍሪን ላይ የተፈጸመው ጥቃት፤ በንፅፅር ሰላማዊ የነበረውን የሶሪያ አካባቢ በጥብጡዋል፤ አይሲስን ለማሸነፍ የተያዘውን ዓለምቀፍ ጥረት ያደናቅፋል። አይሲስና አልቃይዳ አጋጣሚውን ሊጠቀሙበት ይችላሉ ብለዋል።
ባለፈው ሳምንት አፍሪን ውስጥ የቦምብ ድብደባ የጀመረችው ቱርክ ኩርዶች ከሚቆጣጠሩት የሰሜን ሶሪያ አካባቢ ወደሚያገናኛት ድንበር ወታደሮችዋን አዝምታለች።
ጃካርታ ውስጥ ከኢንዶኔዥያ አቻቸው ጋር እየተወያዩ ያሉት ሚኒስትር ማቲስ ቱርክ በምትወስደው ርምጃና በመግለጫዎችዋም መቆጠብን እንድታሳይ አጥብቀን እናሳስባለን ብለዋል።
የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት አባል የሆነችው ቱርክ ጥቃቱን ከመጀመርዋ አስቀድማ ዩናይትድ ስቴትስ እንዳስታወቀች ዕሁድ ዕለት የገለፁት ሚኒስትሩ በዚያ ወቅት የቱርክን ርምጃ እንዳልነቀፉና አነጋገራቸው የተቀየረው በዛሬው መግለጫቸው ላይ መሆኑ ተስተውሏል።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ