ዋሽንግተን ዲሲ —
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የኮቪድ-19 ከትባትን አስገዳጅነት የሚቃወሙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዋሽንግተን ዲሲ ትናንት እሁድ የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል፡፡
የፕሬዚዳንት ባይደን የኮቪድ-19 የማስክና ክትባት ፖሊሲን የተቃወሙት ሰልፈኞች “ፍቅርን እንጂ ግዴታ አትጣሉብን፣ ምርጫን እንጂ ግዴታን አንሻም” የመሳሰሉትን መፈክሮች ያነገቡ መሆኑ ተመልከቷል፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ኮቪድ-19 ከ860ሺ ሰዎች በላይ የገደለ ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት የቆየው ወረርሽኝ በምጣኔ ሀብቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስተከተለ መሆኑ ተነግሯል፡፡
እኤአ ጥር 13 የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ፕሬዚዳንት ባይደን ትላልቅ የንግድ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን መከተባቸውና መመርመራቸውን እንዲያረጋግጡ ያወጡትን ትዕዛዝ መሻሩ ይታወሳል፡፡
ፍርድ ቤቱ የፌደራል መንግሥትን በጀት የሚወስዱ የጤና ተቋማት ግን ትዕዛዙን እንዲያከብሩ ማጽደቁም በወቅቱ ተዘግቧል፡፡
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረግና አለማድረግ የፖለቲካ አቋም መገለጫ እየሆነ መመጣቱም የሚስተዋል ሲሆን በሪፐብሊካን የሚተዳደሩ አብዛኞቹ ግዛቶች የማስክን አስገዳጅነት የማይፈቅዱ መሆኑ ተመልክቷል፡፡