በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በወረርሽኝና በፖለቲካ ሁከት የቀዘቀዘው የማርቲን ሉተር ኪንግ ቀን


የማርቲን ሊተር ኪንግ መታሰቢያ ሀውልት
የማርቲን ሊተር ኪንግ መታሰቢያ ሀውልት

አሜሪካኖች ዛሬ የማርቲን ሊተር ኪንግ መታሰቢያ በአልን እያከበሩ ነው። የዘንድሮው በዓል ግን የሚከበረው በአለም አቀፉ ወረርሽኝ ምክንያት አብዛኞቹ ዝግጅቶች በበይነ መረብ (ኢንተርኔት) አማካኝነት እንዲሆኑ በተደረገበት እና አዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ቃለ መሃላ በሚፈፀሙበት ወቅት ሊኖር ይችላል ተብሎ በሚጠበቅ የፖሊቲካ ሁከት ስጋት ውስጥ ነው።

በየአመቱ ጥር በገባ በሶስተኛው ሰኞ፣ አሜሪካኖች እ.አ.አ በ 1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ ውስጥ የነበረውን መከፋፈል በመቃወም እንዲሁም ለጥቁሮች እኩልነትና የመምረጥ መብት ሲታገል ህይወቱ ያለፈውን የሲቪሎች መብት መሪ ያከብሩታል።

በተለምዶም ቀኑ ኪንግ በህይወት በነበረ ጊዜ የሰራቸውን ስራዎች ለማሰብ ሰዎች የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት ያከብሩት ነበር። ነገር ግን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና በመላው የአሜሪካ ከተሞች ሊፈጠር ይችላል ተብሎ በተሰጋው የፖለቲካ ሁከትና ብጥብጥ ምክንያት የዘንድሮ ክብረበዓል እንደቀድሞው በድምቀት አይከበርም።

የዛሬው ቀን እየታሰበ ያለው ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ቃለ መሃላ ከሚፈፅሙበትና፣ ባለፈው ሳምንት የፕሬዝዳንት ትራምፕ ደጋፊዎች የአሜሪካ ምክር ቤትን ጥሰው በመግባታቸው የአምስት ሰዎች ህይወት በጠፋበት ሁከት ምክንያት፣ 25 ሺህ የአሜሪካ ብሄራዊ ጋርድ ወታደሮች ጥበቃ ከሚያደርጉበት፣ የስልጣን ርክክብ ስነስርዓት ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ነው።

የፌደራል ባለስልጣናት እንደተናገሩት በዚያ ሁከት ውስጥ ከተሳተፉት መሃከል የነጭ አክራሪዎች ይገኙበታል። ተጨማሪ ሁከቶች በዋሽንግተንና ሌሎች ከተማዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉም አስጠንቅቀዋል።

በዚህም ምክንያት የፕሬዝዳንቱ ቃለ መሃላ የሚፈፀምበት ቀን መዳረሻ አንስቶ በዋሽንግተን የሚገኘው ብሄራዊ የመሰብሰቢያ ስፍራ ለህዝብ ዝግ እንዲሆን ተደርጓል፣ የከተማዋ የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎትም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ተደርጓል።

በዛሬው እለት ማርቲን ሉተር ኪንግን በሚዘክረው በዓል ላይ በዋሽንግተን አንዳንድ አካባቢዎች የማህበረሰብ አገልሎቶችን የሚሰጡ የተወሰኑ ስራዎች ቢሰሩም፣ አዘጋጆቹ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የወጡ ርቀትን የመጠበቅ መመሪያዎችና ያለተፈቀዱ አካባቢዎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል። በቨርጂኒያ ክፍለ ግዛት ሬስተን ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች ደግሞ 36ኛውን የኪንግ መታሰቢያ በዓል አካባቢያቸውን በማፅዳትና በመጠለያዎች ውስጥ ለሚኖሩ ቤት አልባ ሰዎች ምሳ በማዘጋጀት አክብረዋል።

ሌሎች ደግሞ ለኪንግ የተዘጋጁት መታሰቢያዎች በድህረ-ገፅ አማካኝነት እንዲሆኑ አድርገዋል። በዋሽንግተን የሚገኘው ፎልጀር ቲያትር ከኪንግ ንግግሮች የተወሰዱ ንባቦችን ሲያቀርቡ የአፍሪካ አሜሪካን ታሪክና ባህል የያዘው ብሄራዊ ሙዚየም ደግሞ በድህረ-ገፅ የሚተላለፍ ነፃ የሙዚቃ ኮንሰርት አዘጋጅቷል።

ማርቲን ሉተር ኪንግ የተወለደበት የጆርጂያ ክፍለግዛት፣ አትላንታ ከተማ የሚገኘውና የተወለደበት መኖሪያ ቤት ያረፈበት ብሄራዊ ፓርክም እንዲሁ በዓሉን በድህረ-ገፅ አማካኝነት አክብሯል። ቦታው የኮሮና ቫይረስ ከጀመረበት ከመጋቢት ወር አንስቶ እስካሁን ለህዝብ ዝግ እንደሆነ ነው።

ኪንግ በህይወት በነበረበት ጊዜ ላካሄዳቸው የሲቭል መብት እንቅሳቃሴዎች ስኬት ዋና ቁልፍ መሰረቱ ሰላማዊ ተቃውሞዎችን ማካሄዱ ነው። ለዚህም ትልቅ አርዓያ የሆኑት የህንድ መሪ የነበሩት ማህተመ ጋንዲ እንደሆኑ ኪንግ ተናግሯል።

ኪንግ ያካሄዳቸው ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች በበርሚንግሃምና አላባማ ፖሊሶች የትምህርት ቤት ተማሪዎች ያደረጉትን ሰልፍ ለመበተን በተጠቀሟቸው ውሻዎችና የእሳት ቱቦዎች ተፈትኗል። በ1965 አላባማ ላይ የተደረገው ሰልፍም ፓሊሶች ባደረሱት ትንኮሳ ምክንያት 'በደም የታጠበው እሁድ' በመባል ይጠራል።

ነገር ግን ሰላማዊና ሁከት አልባ እንቅስቃሴ በማድረግ የፀናው ትግል በ1964 ላይ ውጤት አግኝቶ ፕሬዝዳንት ሊንከን ጆንሰን የዘር ልዩነትን የሚያወግዝ ህግ አፅድቀዋል። ኪንግም የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ ሆኗል።

ኪንግ በ39 አመቱ ህይወቱ ያለፈው በ 1968 ቴኔሲ ክፍለ ግዛት፣ ሜፊስ ከተማ ውስጥ የፅዳት ሰራተኞች መብትን ለማስከበር በተገኘበት ወቅት በተነሳ ሁከት በመገደሉ ነበር።

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡

በወረርሽኝና በፖለቲካ ሁከት የቀዘቀዘው የማርቲን ሉተር ኪንግ ቀን
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:12 0:00


XS
SM
MD
LG