የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ረዳት ዋና ጸሐፊ ማርቲን ግሪፊትስ በኢትዮጵያ ያደረጉትን የአራት ቀናት ጉብኝት ትናንት ሰኞ አጠናቀዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ረዳት ዋና ጸኃፊው ማርቲን ግሪፊትስ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ስለሀገሪቱ ሰብዓዊ ሁኔታዎች እንዲሁም የረድኤት ድርጅቶች ችግር ላይ ላሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እርዳታ ለማድረስ በሚያደርጉት ጥረት የተደቀኑባቸውን ተግዳሮቶች በተመለከተ ገንቢ ውይይቶች ማካሄዳቸዋን መሥሪያ ቤታቸው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ሚስተር ግሪፊትስ በተጨማሪም ከአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ጋር መገናኘታቸውን እና ለያዙት ጥረት ድጋፋቸውን የገለጹላቸው መሆኑ መግለጫው አውስቷል። ከሌሎችም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋማት ተጠሪዎች ጋር በሀገሪቱ ዙሪያ እርዳታ ለማቅረብ ስለሚቻልበት መንገድ መነጋገራቸውን መግለጫው አመልክቷል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ረድኤት ዋና ኃላፊው በመቀሌ ባደረጉት የአንድ ቀን ጉብኝት ከሰብዓዊ ረድኤት አጋር ድርጅቶች ተጠሪዎች እንዲሁም ክልሉን እያስተዳደሩ ያሉትን ባለሥልጣናት በሚቆጣጠሩዋቸው አካባቢዎች በሙሉ የሰብዓዊ ረድኤት ተደራሽነትን መፍቀድ ሲቪሎችን ደህንነት መጠበቅ እና የሰብዓዊ ደህንነት መርኆችን ማክበር እንደሚገባ ያነጋገሩሯቸው መሆኑን መግለጫው አውስቷል። በመቀሌ ቆይታቸው ወሲባዊ ጥቃት ሰላባ የሆኑ ጨመሮ በግጭቶቹ የተጎዱ ሴቶችን እንዳነጋገሩ መግለጫው አክሎ አመልክቷል።
በሀገሪቱ ዙሪያ አጣዳፊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች በሙሉ ማቅረብ ይቻል ዘንድ ሁሉም ወገኖች ያለምንም ገደብ የእርዳታ ሰራተኞች እና አቅርቦቶች ተደራሽነት መፍቀድ ይኖርባቸዋል ያሉት የተመዱ ባለሥልጣን ሆኖም ሰብዓዊ ሁኔታው ይብሱን እንዳያሽቆለቁል ለመከላከል የሚያስችለው ብቸኛው መንገድ ሰላም ሲሰፍን ነው ብለዋል።
(ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ)