ዋግነር ግሩፕ የሚባለው የሩስያ የግል ወታደራዊ ኩባንያ ያሠማራቸው አራት ቅጥር ተዋጊዎችን ማዕከላዊ ማሊ ውስጥ ገድለናል ሲል የአልቃይዳ ቅርንጫፍ አስታወቀ።
ጃማአት ኑስራት አል ኢስላም ዋል ሙስሊሚን የሚባለው ማሊ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ቡድን ትናንት፤ ሰኞ ባወጣው መግለጫ ተዋጊዎቹ ቅዳሜ ዕለት ባንዲያጋራ በሚባለው አካባቢ ከቫግነር ቅጥር ተዋጊዎች ጋር መታኮሳቸውን ገልጿል።
ዋግነር በይፋ የሚታወቅ ተጠሪ ስለሌለው በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን ለማግኘት አለመቻሉን ሮይተርስ ዘግቧል።
ማሊ ባለፉት አሥር ዓመታት ሥር እየሰደደ የመጣውን የእስላማዊ ፅንፈኞች አመፅ ለማስወገድ እየታገለች ስትሆን ሁከቱ ወደ አጎራባች ሀገሮች ተዛምቶ በሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መሰደዳቸው ተዘግቧል።
የሩሲያው ዋግነር ግሩፕ ከማሊ ጦር ጎን ተሰልፈው የሚዋጉ ቅጥር ተዋጊዎን ማዝመት የጀመረው ባለፈው ዓመት ሲሆን የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድኖችና ነዋሪዎች ተዋጊዎቹ ሲቪሎችን በመጨፍጨፍ እየተሣተፈ ነው እያሉ ሲከስሱት ይሰማል።
የሩሲያ መንግሥት የዋግነር ግሩፕ ተቀጣሪዎች ማሊ እንዳሉ ቢያምንም “የማሊ መንግሥት የፀጥታ ጥበቃ ተቀጣሪዎች ሳይሆኑ የሩሲያ ወታደራዊ አሠልጣኞች ናቸው” ብሏል።
ባለፈው ወር የማሊው የአልቃይዳ ቅርንጫፍ ጃማት ኑስራት አል ኢስላም በዋናው የማሊ የጦር ሠፈር ላይ ለደረሰው ጥቃት “የማሊ መንግሥት ከዋግነር ጋር መሥራቱን በመቃወም” መሆኑን በመግለፅ ኃላፊነት መውሰዱ አይዘነጋም።