በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በማሊ ከአራት ዐመት በፊት የታገቱት ኮሎምቢያዊቱ መነኩሲት ተለቀቁ


Pope Francis with former Mali captive nun Gloria Cecilia Narvaez
Pope Francis with former Mali captive nun Gloria Cecilia Narvaez

ማሊ ውስጥ እ አ አ በ2017 በጽንፈኛ እስላማዊ ታጣቂዎች የተጠለፉት ኮሎምቢያዊቱ መነኩሲት ትናንት ቅዳሜ መለቀቃቸውን የማሊ ፕሬዚደንት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ለአራት ዐመት ከስምንት ወር ታግተው የቆዩትን ሲስተር ግሎሪያ ሴሲሊያ ናርቬዝን "ጀግና" ሲል ከፕሬዚደንቱ ጽህፈት ቤት በትዊተር የወጣው መግለጫ አሞግሷቸዋል።

ሲስተር ናቫሬዝ እ አ አ 2017 ዐመተ ምህረት የካቲት መጀመሪያ ላይ የተጠለፉት ከማሊ ዋና ከተማ ከባማኮ አራት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ኩቱሊያ የተባለ አካባቢ ሚስዮናዊ ስራ ላይ ሳሉ እንደነበር ተገልጿል።

የባማኮ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ዣን ዜርቦ ስለመነኩሲቷ መለቀቅ የማሊን መንግስት አመስግነው፥ በመልካም የጤና ሁኔታ ላይ እንዳሉ ገልጸዋል። ቤተሰቦቻቸውም ያናጋገሩዋቸው መሆኑን በመግለጽ መለቀቃቸውን አረጋግጠዋል።

የማሊው ወታደራዊ መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ ባወጡት መግለጫ ሌሎቹንም ታጋቾች በሙሉ ለማስለቀቅ ጥረታችንን ቀጥለናል ሲሉ የማሊን ህዝብ እና ዐለም አቀፉን ማህበረሰብ አሳውቀዋል።

" እንዲለቀቁ ብዙ ጸልየናል፥ የማሊን መንግሥት እና ሌሎቹንም ለመለቀቅ ያበቋቸውን መልካም ሰዎች በሙሉ እናመሰግናለን" ብለዋል። የሲስተር ናቫሬዝ ወንድም በበኩላቸው የእህታቸው ፎቶግራፍ ተልኮላቸው እንዳዩ እና በጥሩ ሁኒታ ላይ እንዳሉ ተናግረዋል።

ሲስተር ናቫሬዝ ስላሉበት ሁናቴ በየጊዜው የተለያዩ መረጃዎች ይሰሙ የነበረ ሲሆን በዚህ የአውሮፓ 2021 ዐመተ ምህረት መጀመሪያ ከጠላፊዎቻቸው እጅ ያመለጡ ሁለት አውሮፓውያን በደህና ሁኔታ ላይ እንዳሉ ተናግረው ነበር።

ማሊ እ አ አ ከ2012 ዐመተ ምህረት ጀምሮ በሰሜናዊ ግዛቶቹዋ የተቀሰቀሰውን አክራሪ እስላማዊ አመጽ ለመቆጣጠር ስትጣጣር የቆየች ሲሆን አመጹ ባሁኑ ወቅት ወደአጎራባች ቦርኪና ፋሶ እና ኒዠር ተዛምቷል። በሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታው እየተባባሰ በመሄዱም ጠላፋዎች በተደጋጋሚ ይፈጸማሉ።

XS
SM
MD
LG