የማሊ እና የቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ መንግሥታት ልዑካን ኒያሚ የገቡት በዚያች አገር በቅርቡ የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ከመሩት ወታደራዊ ኃይል አባላት ጋር ተገናኝተው ለመነጋገር መሆኑ ታውቋል።
የሁለቱ አገሮች ወታደራዊ መሪዎች የመጓዛቸው ዜና የተሰማው፤ የኒዠር ወታደራዊ ጁንታ መሪዎች የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ወደ ሥልጣን ይመልሱ ዘንድ፡ ያቀረበላቸውን ጥሪ ውድቅ ማድረጋቸውን ተከትሎ የምዕራብ አፍሪቃ አገራት የምጣኔ ሃብት ማኅበረሰብ (ኤኮዋስ) በጉዳዩ ላይ ለመምከር ለተነገ ወዲያ ሃሙስ ቀጠሮ በያዙበት ወቅት ነው።
የመንግሥት ግልበጣው መሪዎች እስካለፈው እሁድ ሃምሌ 30፣ 2015 ዓም የመንግሥቱን ስልጣን ለቀድሞው የሃገሪቱ መሪዎች መልሰው እንዲያስረክቡ፤ ያ ካልሆነ ግን ወታደራዊ እርምጃ እንደሚጠብቃቸው ኤኮዋስ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ቸል በማለት፤ የአገሪቱን የአየር ክልል በመዝጋት ሊቃጣ የሚችለውን ማንኛውንም ጥቃት ‘እንከላከላለን’ ሲሉ ዝተዋል።
በሌላ በኩል፡ እስር ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳንት መሃመድ ባዙም ተለቀው ወደ ሥራቸው ካልተመለሱ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ
መስማማታቸውን ባለፈው አርብ ይፋ ያደረጉት የኤኮዋስ የመከላከያ ኃላፊዎች፤ ተግባራዊነቱ አስመልክቶ ግን ውሳኔው የሃገራቱ መሪዎች እንደሚሆን አመልክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፡ የሁለት የቡድኑ አባል አገራት፡ የማሊ እና የቡርኪና ፋሶ ወታደራዊ ጁንታ መሪዎች “ካስፈለገ ከኒዠር ጎን እንሰለፋለን” ማለታቸውን ተከትሎ ሕብረቱ ክፍፍል ገጥሞታል። በተጨማሪም ሁለቱ አገሮች ለኒዠር አጋርነታቸውን ለማሳየት “የልዑካን ቡድን ወደ ኒያሚ ልከዋል” ሲል የማሊ ጦር ሰራዊት በትላንትናው ዕለት በማህበራዊ ሚዲያ ገጹ ይፋ አድርጓል። በማስከተልም የልዑካን ቡድኑ ተወካይ አገራቸው ለወታደራዊ ጁንታው የምትሰጠውን ድጋፍ በድጋሚ አረጋግጠዋል።
መድረክ / ፎረም