በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የማላዊ የቀድሞ ም/አፈጉባኤ ራሳቸውን ገደሉ


የቀድሞ የማላዊ ከፍተኛ ህግ አውጭ የምክር ቤት አባል በምክር ቤቱ ህንጻ ውስጥ ራሳቸውን ገደሉ፡፡

በምክር ቤቱ የቀድሞ ምክትል አፈጉባኤ የነበሩት የ50 ዓመቱ ክሌመንት ቺዋያ ትናንት ሀሙስ ከሰዓት በኋላ በምክር ቤቱ ህንጻ ውስጥ ራሳቸውን በሽግጥ ተኩሰው መግደላቸው በአገሪቱ ምክር ቤት ውስጥ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡

ብላንታየር ውስጥ የሚኖሩት የቀድሞ ወታደራዊ መኮንና የደህንነት ባለሙያ ሸሪፍ እንዲህ ይላሉ

“እኔ የምለው ምክር ቤትን የሚያህል ትልቅ ተቋምን ደህንነት በመጠበቅ ላይ ቸልተኝነት አለ፡፡ የደህንነቱን አስተዳዳር አስመልክቶ ይህ የማንቂያ ደወል ነው፡፡ ካሜራና የመፈተሻ መሳሪያዎች እያሉ የደህንነት ጥበቃን በዚያ መንገድ መምራት አይቻልም፡፡”

ቺዋያ ራሳቸውን የገደሉበት ምክንያትና ዝርዝር በተገቢው ጊዜ ለህዝብ እንደሚገለጽ ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ዩናይትድ ዴሞክራቲክ ፍሮንት የሚባለው ተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የነበሩት ቺዋያ በቅርቡ በገጠማቸው የተሽከርካሪ አደጋ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የነበረ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ተሽከርካሪው የምዝገባ ጊዜ ያለፈበትና ንብረትነቱም ለሌላ ሰው የተላለፈ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

ቺዋያ የመንግሥት ኃላፊዎች በፍርድ ቤቱ ጉዳይ ጣልቃ ገብተው እንዲረዷቸው ፈልገው የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ግን የተለየ ውሳኔ ማስተላለፉም ታውቋል፡፡

የቀድሞ የምክር ቤት አባል መሳሪያ ይዘው እንዴት ወደ ህንጻው ሊገቡ ቻሉ የሚለው የደህንነት ጥያቄ በምክር ቤቱ አባላት ዘንድ ተነስቷል፡፡

XS
SM
MD
LG