በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“ፈረንሳይ በአፍሪካ ላይ ያላት ተጽዕኖ አክትሟል” ማክሮን


የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፤ የጋቦን ፕሬዚዳንት አሊ ቦንጎ ኦንዲምባ
የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፤ የጋቦን ፕሬዚዳንት አሊ ቦንጎ ኦንዲምባ

“ፈረንሳይ በአፍሪካ ላይ ያላት ተጽዕኖ አክትሟል” ሲሉ አራት የአፍሪካ አገራትን በመጎብኘት ላይ የሚገኙት የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዛሬ ተናግረዋል፡፡

በቀድሞ የፈርንሳይ ቅኝ ግዛቶች ጸረ-ፈረንሳይ አቋሞች እየተጠናከሩ ነው፡፡ ይህም ሩሲያና ቻይና ያላቸው ተጽእኖ እየጨመረ በመምጣቱ አህጉሪቱ የዲፕሎማሲ ጦር ሜዳ በመሆኗ ነው ተብሏል፡፡

በተፈጥሮ አካባቢ ላይ በሚያተኩር ስብሰባ ላይ ለመካፈል ጋቦን የተገኙት ማክሮን፣ ፈረንሳይ በአፍሪካ ላይ ጣልጋ የመግባት የቀድሞ ፖሊሲዋ አትመለስም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

“የፍራንስ አፍሪክ ዘመን አክትሟል” ብለዋል በመዲናዋ ሊበርቪል ለተሰበሰቡ የፈረንሳይ ማኅበረሰብ አባላት ባደረጉት ንግግር፡፡ ይህም ፈረንሳይ ጥቅሟን ለማስከበር ስትል ፈላጭ ቆራጭ መሪዎችን ስትደግፍ የቆየችበትን ፖሊስ ያመለከተ ነው ሲል ኤኤፍፒ በዘገባው አመልክቷል፡፡

አፍሪካውያኑ በ1960 ዎቹ ከቅኝ ግዛት ነጻ በወጡበት ወቅት የተፈጥሮ ሃብታቸውን ለመጠቀምና ወታደራዊ ጣቢያ ለማቋቋም ስትል ፈረንሳይ በ‘ፍራንክአፍሪክ’ ፖሊሲዋ መሠረት በቀድሞ ቅኝ ግዛቷ ፈላጭ ቆራጭ መሪዎች እንዲፈጠሩ አድርጋለች ሲል አክሏል የኤኤፍፒ ዘገባ፡፡

ማክሮን ጉብኝታቸውን ከመጀመራቸው ቀደም ብሎ ባለፈው ሰኞ ሲናገሩ፣ በመጪዎቹ ወራት በግልጽ በሚታይ ሁኔታ ፈረንሳይ በአፍሪካ ያላትን የወታደሮች መጠን ትቀንሳለች ብለዋል፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት ፈረንሳይ የቀድሞ ቅኝ ግዛቷ ከነበሩት ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ እና ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ወታደሮቿን አስወጥታለች፡፡

በሴኔጋል፣ አይቮሪ ኮስት፣ ጋቦን እና ጂቡቲ ከ3 ሺህ በላይ ወታደሮች እንዳሏት ኦፊሴላዊ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

XS
SM
MD
LG