"ፈረንሣይ እስላማዊ አማጺያንን ለመታገል ወታደሮቿን ለዐሥርት ዓመታት ለማሠማራቷ የአፍሪካ ሀገራት ምስጋና አላቀረቡም" ብለው ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን መናገራቸው በአፍሪካ በሚገኙ አጋሮቻቸውና በፈረንሣይ በሚገኙ ለዘብተኞች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል። የማክሮን ንግግር "የቅኝ ገዢዎች አስተሳሰብ ነው" የሚል ነቀፋም ገጥሞታል።
ማክሮን ሰኞ ዕለት ለፈረንሣይ አምባሳደሮች ባደረጉት ንግግር፣ “ይመስለኛል እናመሰግናለን ማለቱን ረስተውታል። ወደፊት ያደርጉት ይሆናል” ሲሉ ተደምጠዋል። ወታደሮቻቸውን ማሠማራታቸው ትክክለኛ ርምጃ እንደነበርና፣ ጣልቃ ባይገቡ ኖሮ በሳህል የሚገኙ ሀገራት ሉአላዊነታቸውን ጠብቀው ሊቆዩ እንደማይችሉም ማክሮን ጨምረው ተናግረዋል።
በሳህል ቀጠና የተገኙት ሀገራቱ በጠየቁት መሠረት እንደሆነና ለቀው የወጡትም በተደረጉት መፈንቅለ መንግሥታት ምክን ያት እንደሆነ፣ ለመፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎች ፈረንሣይ ድጋፍ መስጠት እንደማትሻም ማክሮን ተናግረዋል።
በሳህል ቀጠና በሚገኙ ፈረንሣይኛ ተናጋሪ ሀገራት ውስጥ ባለፉት አራት ዓመታት ተከታታይ መፈንቅለ መንግሥት መደረጉን ተከትሎ የፈረንሣይ ሚና ቀንሶ ወታደሮቿ ከአንዳንዶቹ ሃገራት ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል።
ሩሲያ፤ በማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኒዤር ፈረንሣይን በመተካት ተጸኖዋን ስታሳርፍ፣ ፓሪስ ደግሞ ከሴኔጋል እና ከቻድ ጋራ የቀረበ ግንኙነት እንዲኖራት ብትሞክርም፣ ሁለቱ ሃገራት ግን የፈረንሣይ ጦር እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ፈረንሣይ በፕሬዝደንት ፍራንሷ ኦላንድ የሥልጣን ዘመን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2013 ዓ.ም በማሊና በሳህል ቀጠና እስላማዊ አማፂያንን ለመዋጋት ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯ ይታወሳል። በወቅቱ 58 ወታደሮቿ ሕይወታቸውን አጥተዋል።
መድረክ / ፎረም