በፍሎሪዳው ማክዲል አየር ኃይል ጦር ሰፈር ተገኝተው በሥልጣን ዘመናቸው መጨረሻ፣ ብሔራዊ ደኅንነትን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር፣ ዩናይትድ ስቴትስ እስላማዊ መንግሥት ነኝ ባዩን አማጺ ቡድን ከማዳከሟም በላይ፣ ከነፍሰ-ገዳዮችና ከጨካኞች ጋር የሚተካከል ተግባሩ እንዲገታል በተለይም መሪው ኦሳማ ቢን ላደን በመገደሉ አል-ቃዒዳ ጥጉን እንዲይዝ እንደተደረገ አመልክተዋል።
አሜሪካውያን፣ አገራቸው ሽብርተኛነትን ለማሸነፍ የተያያዘችውን ጎዳና እንዲቀጥሉም፣ ኦባማ አሳስበዋል።
ፕሬዚደንት ኦባማ በማክዲል አየር ኃይል ጦር ሰፈር ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በእስያ ያሉ ሸሪኮችን ላካተተው አዲስ ስትራተጂ ምስጋና ይግባውና፣ ሽብርተኛነትን በማዋጋት እረገድ አስተዳደራቸው ስኬታማ ሥራ አከናውኗል።
"ሸክሙን ሁሉ ዘመቻ ላይ ለሚገኘው እግረኛ ጦር አሳልፎ ከመስጠት ይልቅ፣ ሽብርተኞች ባሉበት አካባቢ ሁሉ አሰሳ ከማድረግ ይልቅ፣ የአጋሮች መረብ ልንዘረጋ ችለናል።"
አል-ቃዒዳ፣ በተለይም መሪው ኦሳማ ቢን ላደን ከተገደለ ወዲህ፣ በቀደሙ ምስሉ ግን እርቃኑን የሚንቀሳቀስ ሆኗል ያሉት ኦባማ፤ እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው ነውጠኛ ቡድንም፣ በተለይ ዩናይትድ ስቴትስና ሸሪኮቿ የቡድኑን የገቢ ምንጫ ካዳከሙ ጀምሮ ተሽመድምዶ፣ ወጣቶችን የሚያማልልበት ኃይሉም ተንኮታኩቶ ወድቋል ሲሉ ተናግረዋል።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡