በከፍተኛ የሀገር ክህደት ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ የነበሩት የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ኤሌክትሮኒክስ ሳይበር መምሪያ ኃላፊ ሜ/ጀ ገብረመድህን ፍቃዱ በእስር ላይ እያሉ ትናንት ሰኞ ሚያዝያ 24/2014 ዓ.ም ሕይወታቸው ማለፉ ታውቋል።
የሜ/ጀ ገብረመድህን ሕይወት ማለፍን ተከትሎ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ትናንት በፌስቡክ ገጹ ባወጣው አጭር መግለጫ፣
“ከረፋዱ ሦስት ሰዓት ተኩል አካባቢ በቤተሰብ ጥየቃ ሰዓት ባለቤታቸው እና ልጃቸው አስጠርተዋቸው እያወሩ እያለ በድንገት በመውደቃቸው ወዲያውኑ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ሕክምና ቦታ ቢወሰዱም ህይታቸው አልፏል” ሲል አስታውቋል።
በጉዳዩ ላይ ቪኦኤ ያነጋገራቸው የፍትህ ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ፍቃዱ ጸጋ፤ “እኔም ትናንት ጠዋት ነው ከፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን መረጃውን ያገኘሁት” ብለዋል። ሜ/ጀ ገብረመድህን ፍቃዱ በድንገት ከወደቁ በኋላ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ወደ ሕክምና ማዕከል መወሰዳቸውንና ባሉበት ሕይወታቸው ማለፉን መረዳታቸውን ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል መንግሥት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ በሜጀር ጀነራል ሕይወት ማለፍ የተሰማውን ሐዘን ገልጾ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል። በዋናነት “የፌዴራል መንግሥት የወሰዳቸው እርምጃዎች ማንነትን ያነጣጠረ ነው” ያለው መግለጫ አክሎም የህልፈታቸው መንስኤ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠይቋል።
የፍትህ ሚኒስትር ዴዔታው አቶ ፍቃዱ ጸጋ በትግል ስማቸው ወዲ ነጮ በመባል የሚታወቁት ሜጀር ጀነራል ገብረመድህን ፍቃዱ፣ ለሞት የተዳረጉት በምን ምክንያት እንደሆነ እስካሁን አለመታወቁን ገልፀው ለዚህም የአስከሬን ምርመራ በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ሟቹ ከዚህ ቀደም ይከታተሉት የነበረ ሕክምና ይኖር እንደሆን የተጠየቁት አቶ ፍቃዱ “አይናቸውን ይታከሙ ነበር” የሚል መረጃ እንዳላቸው ገልፀዋል። ከዛ ውጭ ሌላ የሕክምና ሂደት ውስጥ እንደነበሩ የሚያሳይ መረጃ እንደሌላቸው እና ከማረሚያ ቤትም ባጣሩት መሰረት የተለየ መረጃ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልፀዋል።
የሜጄር ጄኔራሉን ሕልፈተ ሕይወት በተመለከተ ከቤተሰቦቻቸው እና ከጠበቃቸው መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሊሳካልን አልቻለም፡፡ ሜጀር ጀነራል ገ/መድህን ፍቃዱ፣ የመከላከያ ሚኒስቴር የኮሚኒኬሽን ኤሌክትሮኒክስ ሳይበር መምሪያ ኃላፊ በነበሩበት ወቅት፣ ጥቅምት 24/2013 ዓ/ም መከላከያ ሰራዊቱ ከሰሜን ዕዝ ጋር የነበረውን የሬዲዮ ግንኙነትን በማቋረጥ እንዲሁም የሬዲዮ መገናኛ መሳሪያ ለህወሓት ወታደራዊ ቡድን አሳልፈው ሰጥተዋል በሚል በዓቃቤ-ህግ የቀረበባቸውን ከፍተኛ የሀገር ክህደት ክስ ሂደት በመከታተል ላይ ነበሩ፡፡
በቀድሞ የመከላከያ መኮንኖች የክስ መዝገብ ላይ 1ኛ ተከሳሽ የሆኑት ሜጀር ጀኔራሉ ሕይወታቸው በድንገት ማለፉን ተከትሎ በሌሎች ተከሳሾች ላይ የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን የፍትህ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረሽብርና የህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ቀሪ የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለዛሬ ተይዞ በነበረው ተለዋጭ ቀጠሮ፣ 7ኛ እና 15ኛ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች ቃላቸውን ለመስጠት ተገኝተው ቃለ መሀላ ፈፅመው ነበረ ብሏል ሚኒስቴሩ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ፡፡
ይሁንና የ1ኛተከሳሽ ድንገተኛ ሕልፈተ ሕይወትን ተከትሎም በክስ መዝገቡ የተካተቱ ሌሎች ተከሳሾችና የተከሳሽ ጠበቃ የሟች አስከሬን ባልተቀበረበት ሁኔታ ዐቃቤ ህግ የሚያሰማብንን ምስክሮች ለመከላከል የሚያስችል የስነ ልቦና ዝግጅት ስለሌለን ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን ሚል ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ፣ ቀሪ የዐቃቤ ህግ ምስከሮችን ለመስማት ከግንቦት 08 እስከ ግንቦት 12/2014 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱን ገልጿል፡፡
በመዝገቡ የተካተቱት ሌሎች ተከሳሾች አጃቢ ተመድቦልን በቀበር ሥነ ስርዓቱ ላይ እንድንገኝ ለማረሚያ ቤት ደብዳቤ ይፃፍልን ሲሉም ፍርድ ቤቱን የጠየቁ ሲሆን፣ ዐቤ ሕግ በበኩሉ ሁኔታው “ያልተለመደና ለደህንነት አስጊ” መሆኑን ገልፆ ማረሚያ ቤትም ጉዳዩን ቢመለከተው መልካም ነው ሲል ማሳወቁ ተመላክቷል።
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የፀረ ሽብርና የህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በፅ/ቤት ከተወያየ በኋላ በፅ/ቤት በኩል ትዕዛዝ እንደሚሰጥበት ገልጾ፣ ሌሎቹ ተከሳሾች በቀብሩ ላይ ለመገኘት ያላቸውን ፍላጎት በፅሑፍ እንዲያቀርቡና መወሰኑንም ነው ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡