በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የስደተኞች የረቡዕ ውሎ በሊብያ


ለስደተኞች የሊብያ ረቡዕ ከሌላው ቀን የተሻለ ለውጥ የታየበት አልነበረም፡፡

ዛሬም ሥጋት ነበር፡፡ ዛሬም ግድያዎች ነበሩ - ስደተኞቹ እንደሚሉት፡፡ ሦስት ቻዳዊያን (ሁለት ወንዶች እና አንዲት ሴት ስደተኞች) በቆዳቸው ቀለም ምክንያት ብቻ ጎዳና ላይ መገደላቸውን ገልፀዋል፡፡

ከሌላው ቀን የተለየ ነገር ቢኖር ስደተኞቹን የጎበኘ የቀይ መስቀል ቡድን የነበረ ቢሆንም "የምንወስደው የመንግሥታቱ ድርጅት የምዝገባ ወረቀት ያላቸውን ነው፤" ይሉ እንደነበር አንዳንድ ስደተኞች ገልፀዋል፡፡ የተባለው ወረቀት ያላቸው ቢኖሩም ወደግብፅ ለመሄድ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ መንግሥት ስደተኞቹ ወደእነዚያ ሃገሮች ከሄዱልኝ አነሣቸዋለሁ ማለቱን በመስማታቸውና በኃይል እንወሰዳለን ብለው በመሥጋታቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ሊብያ ውስጥ ኤምባሲ እንደሌለው ጠቅሶ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያንና እርዳታ የሚሹ የኤርትራና የሌሎችም ሃገሮች ዜጎች ቢኖሩ ትሪፖሊ በሚገኘው የሱዳን ኤምባሲና ቤንጋዚና ኩፍራ በሚገኙ የሱዳን ቆንስላ ፅ/ቤቶች እንዲመዘገቡ አሳስቦ የስልክ ቁጥሮችን ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባል አምባሣደር ዲና ሙፍቲ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ማብራሪያ ስደተኞቹን ከአካባቢው የሚያነሷቸው ወደ ግብፅ ወይም ወደ ሱዳን ከተጓጓዙ በኋላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በሊብያና በአይቮሪ ኮስት አጣዳፊ ቀውሶች ውስጥ የተጠመዱት ብዙ ሺህ ሲቪሎች ያሉበት አደገኛ ሁኔታ በጥልቅ እንዳሳሰባት የገለፀችው የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር የበጎ ፍቃድ አምባሣደር አንጀሊና ጆሊ ዓለም ፈጥኖ ሊደርስላቸውና ደህንነታቸውም ሊጠበቅ እንደሚገባ፤ ካስፈለገም የሚወጡበት፣ ጥገኝነታቸውም የሚረጋገጥበት ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ተማፅኖ አሰምታለች፡፡

ጆሊ ይህንን ጥሪዋን ያስተላለፈችው ከስደት ወደሃገራቸው ተመልሰው አሥር ዓመት እና ከዚያ በላይ ቢያስቆጥሩም ከሕብረተሰቡ ጋር የመቀላቀል ችግር ያለባቸውን የቀድሞ ስደተኞች ሁኔታ ለማዳመጥ ከተጓዘችባት አፍጋኒስን ዋና ከተማ ካቡል ነው፡፡

ለዝርዝሩና ለተጨማሪ መረጃ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG