የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ በተሾሙ በስድስት ሳምንታቸው ሥልጣናቸውን እንደሚለቁ ዛሬ ከጥቂት ሰዓታት በፊት አስታወቁ። የምጣኔ ሃብት ፕሮግራማቸው ገበያው ላይ በፈጠረው ቀውስና የወግ አጥባቂ ፓርቲያቸውን በመከፋፈሉ ነው ተብሏል።
ሮይተርስ ከለንደን እንደዘገበው፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ አዲስ መሪ ይመረጣል።
ቴን ዳውኒንግ ስትሪት ከተባለው የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ደጃፍ ላይ ሆነው የተናገሩት ሊዝ ትረስ የፓርቲያቸውን ትምምን ማጣታቸውን እና በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት የገቡትን ቃል በተግባር ለመተርጎም አለመቻላቸውን አምነዋል።
“በመሆኑም ለግርማዊነታቸው ንጉሥ (ቻርለስ) ከፓርቲ መሪነቴ መልቀቄን አሳውቄያቸዋለሁ” ብለዋል ትረስ።