በሊብያ ያለው የኢትዮጵያዊያንና የኤርትራዊያን ሕይወት እጅግ አሣሣቢ መሆኑ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ማምሻውን ወደ ቤንጋዚ ደውዬ ዳንኤል መንግሥቱ የሚባል በቀን ሥራ ይተዳደር የነበረ ኢትዮጵያዊ አግኝቼ አነጋግሬ ነበር፡፡
ዳንኤል ብዙ ስደተኞች በአንድ አዳራሽ ውስጥ ታጭቀው እንደሚገኙ፤ ብዙዎች ደግሞ መጠለያ አጥተው ሜዳ ላይ መበተናቸውን አጫውቶኛል፡፡ ብዙ ሴቶች ደግሞ ነፍሰጡሮች ሳይቀሩ አደጋ ይደርስብናል ብለው በመፍራት እግራቸው ወደ ወሰዳቸው አቅጣጫ ሁሉ መበተናቸውን ነግሮኛል፡፡
ምግብና ውኃ የሌላቸው ስደተኞች ለረሃብና ለመጎሣቆል ተጋልጠዋል፤ ወደ መሃል ከተማ የወጡትም ያልተመለሱ ብዙ እንደሆኑ ዳንኤል ይናገራል፡፡
እስከአሁን የደረሰላቸው እርዳታና ድጋፍ አለመኖሩን የሚገልፀው ዳንኤል ጠንካሮቹ መንግሥታትና ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች ዜጎቻቸውን በመርከብ ሲያስወጡ እነርሱ ግን እየተመረጡ እዚያው ችግር ውስጥ መቅረታቸውን ገልፆልኛል ዳንኤል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ ሌሎች አካላት ፈጥነው እንዲደርሱላቸው እየተማፀነ ነው፡፡
እንዲሁም ወደ ጄኔቫ የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ዋና ፅ/ቤት ዛሬም ማምሻውን ደውዬ የኮሚሽነሩን ቃል አቀባይ ሚስ ሲቤላ ዊልክስን አነጋግሬ ነበር፡፡ የተጠናከረ ሥጋታቸውን ነው ዛሬም የገለፁት፡፡
ሊብያ ውስጥ ወደ ሃያ የሚሆኑ የመሥሪያ ቤታቸው ባልደረቦች ትሪፖሊ ውስጥ እንደሚገኙ ሚስ ዊልክስ አመልክተው እነርሱም እራሣቸው ያሉት ለአደጋ ተጋልጠው ቢሆንም የቻሉትን እያደረጉ መሆናቸውን፣ ሃያ አራት ሰዓት ክፍት የሆነ የስልክ መሥመር እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡
ለተጨማሪና ለዝርዝሩ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡