በሊቢያ የሚገኘው ትልቁ ነዳጅ አምራች ኩባንያ በተቃዋሚ ሰልፈኞች በተደረገበት ጫና ምክንያት ለመዝጋት መገደዱን አስታውቋል።
በአገሪቱ የተከሰተውን የነዳጅ እጥረት ተከትሎ፣ ኡባሪ በተሰኘችው በረሃማ ከተማ ያሉ ነዋሪዎች በሻራር የሚገኘው የነዳጅ ማምረቻ መስክ እንዲዘጋ ማስገደዳቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃንን ጠቅሶ የአሶስዬትድ ፕረስ ዜና ወኪል ዘግቧል።
በመንግሥት የሚተዳደረው ብሔራዊ የነዳጅ ኮርፖሬሽን፣ በተደረገበት ጫና ምክንያት የኮንትራት ግዴታውን መወጣት እንዳልቻለ አስታውቋል። በመሆኑም በሜዲትሬንያን ባህር ዳርቻ ወደምትገኘው ዛዋይ ማጣሪያ ጣቢያ ይልክ የነበረውን ድፍድፍ ነዳጅ ለማቆም መገደዱን ገልጿል። ከተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ጋር ድርድር በመደረግ ላይ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል።
ሊቢያ በቀን ከ1.2 ሚሊዮን በርሜል በላይ ነዳጅ የምታመርት ሲሆን፣ ሻራር የሚገኘው የነዳጅ መስክ የአገሪቱ ትልቁ ማምረቻ፣ 300 ሺሕ በርሜል የማምረት አቅም አለው።
በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የተደገፈ አመጽ፣ የአገሪቱ የረጅም ግዜ መሪ ሞአመር ጋዳፊን ከሥልጣን ካስወገደ ወዲህ፣ በምሥራቅ እና ምዕራብ የሚገኙ ተቀናቃኝ ኃይሎች አገሪቱን ለሁለት ከፍለው በማስተዳደር ላይ ናቸው።
የተቀናቃኝ ወገኖች እና የውጪ ኃይሎችም በአፍሪካ ትልቅ እንደሆነ የሚነገርለትን የነዳጅ ሃብቷን ለመቆጣጠር ፍጥጫ ላይ ናቸው።
መድረክ / ፎረም