በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሲቪሎች ዴርና እንዳይገቡ ተከለከሉ


ባለፈው ዕሁድ በከባድ ጎርፍ ወደ ተመታችው ምሥራቃዊዊቱ የሊቢያ ከተማ ዴርና
ባለፈው ዕሁድ በከባድ ጎርፍ ወደ ተመታችው ምሥራቃዊዊቱ የሊቢያ ከተማ ዴርና

ባለፈው ዕሁድ በከባድ ጎርፍ ወደ ተመታችው ምሥራቃዊዊቱ የሊቢያ ከተማ ዴርና ሲቪሎች ዛሬ እንዳይገቡ መከልከላቸው ተነገረ።

ሲቪሎች ወደ አካባቢው እንዳይገቡ የተከለከለው የአሰሳና የነፍስ አድን ሠራተኞች በፈራረስችውና ጭቃ በለበሰችው ከተማ ውስጥ የሚያደርጉትን ጥረት እንዳያደናቅፉ መሆኑን አሶሲየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

በጎርፉ የሞተው ሰው ቁጥር ወደ 11 ሺህ 300 ሲያሻቅብ አሥር ሺህ የሚደርስ ደግሞ የደረሰበትር አለመታወቁን የሊቢያ ቀይ ጨረቃ አመልክቷል።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት የሦስት ሺህ አስከሬኖች ቀብር መፈፀሙንና ለተጨማሪ ሁለት ሺህ ደግሞ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን የሃገሪቱን የጤና ሚኒስትር ኦትማን አብዱልጃሊል አስታውቀዋል።

የሟቹ ቁጥር ሃያ ሺህ ሊደርስ እንደሚችል የዴርና ከንቲባ አብዱልመናም አል-ጋይቲ ለአረቢያ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

እጅግ በበረታ ዶፍና በግድቦች መደርመስ ምክንያት በተከተለው ጎርፍ የከፋው ጉዳት የደረሰባት ዴርና ማጥ ሥር ከመዋሏና ህንፃዎቿም ከመፈራረሳቸው በተጨማሪ ነዋሪዋም በውኃው ተወስዶ ወደ ባህር መቀላቀሉ ተወርቷል።

ነዋሪዎች ከባህር ዳርቻ አካባቢዎች እንዲሸሹ ከጎርፉ አንድ ቀን በፊት፣ ባለፈው ቅዳሜ፣ የምሥራቅ ሊቢያ ባለስልጣናት ትዕዛዝ አስተላልፈው የነበረ ቢሆንም ስለ ግድቦቹ ግን ምንም የሰጡት ማስጠንቀቂያ እንዳልነበረ ተገልጿል።

በዚሁ ወጀብ በሌሎች የምሥራቃዊ ሊቢያ አካባቢዎችም 170 ሰዎች መሞታቸውን የጤና ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት፣ የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማኅበራት ዓለምአቀፍ ፌዴሬሽን፣ ዓለምአቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ዛሬ በጋራ ባወጡት መግለጫ አስከሬን ለመቅበር የሚታየው ወከባና ጥድፊያ ሊያስከትሉ በሚችሏቸው የህግና ስሜታዊ መዘዞች ምክንያት ገታ እንዲደረግ አስጠንቅቀዋል።

ለ250 ሺህ ሊቢያዊያን አስቸኳይ እርዳታ ለማድረስ 71 ሚሊየን ዶላር በአጣዳፊ እንደሚያስፈልገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰብአዊ አገልግሎት ቢሮ አስታውቋል።

884 ሺህ የሚሆን ሰው በዝናብና በጎርፍ በቀጥታ በተጎዱ አካባቢዎች እንደሚኖር ቢሮው አክሎ አመልክቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG