በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዕውቁ ኢትዮጵያዊ ሃኪም ፕሮፌሰር እደማሪያም ጸጋ አረፉ


ፕሮፌሰር እደማሪያም ጸጋ አረፉ
ፕሮፌሰር እደማሪያም ጸጋ አረፉ

"ፕሮፌሰር እደማሪያም በግል ጥረታቸው የድሕረ ምረቃ የሕክምና ትምሕርት ፕሮግራሞች እንዲከፈት ያደረጉ ናቸው።" ከቀድሞ ተማሪዎቻቸው አንዱ ፕሮፌሰር ጌታቸው አደራዬ። “ለሕመምተኛና ለተማሪ ከፍ ያለ ክብር የሚሰጥ፤ ጥሩ ተማሪ የሚያፈራና ከእርሱ የተሻሉ እንዲሆኑ የሚያደርግ፤ ተማሪ ሆነን 'ተሳስተሃል' ብለን ደፍረን እንድናገረው የሚያበረታታን ፕሮፌሰር፤ ለሞያው የረቀቀ ክብር ያለው ‘ሃኪም’ የሚለው መጠሪያ ለእርሱ የተጻፈ የሚመስል ባለሞያ ነበር።” ዶ/ር አሰፋ ጄጃው።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሕክምና ሞያ ታሪክ ልዩ ሥፍራ ከሚሰጣቸው የሕክምና ባለሞያዎችና መምሕራን አንዱ: አንጋፋው ሃኪም ፕሮፌሰር እደማሪያም ጸጋ በተወለዱ በ77 ዓመታቸው ከትናንት በስተያ ሰኞ ታሕሳስ 23, 2010 ዓ.ም. ከሃያ ሦሥት ዓመታት በላይ በኖሩባትና በሞያቸው ባገሉባት የካናዳዋ ሃሚልተን ከተማ አርፈዋል።

ከአባታቸው ሊቀ ካህናት አለቃ ጸጋ ተሻለ እና ከእናታቸው ወ/ሮ የተመኝ መኮንን ሰኔ 30, 1929 ዓም በጎንደር ከተማ ልዩ ስሙ ባሕታ በተባለ ሥፍራ የተወለዱት እደማሪያም የመጀመሪያ ደረጃ ትምሕርታቸውን በዚያው በጎንደር ከተማ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ተከታትለዋል።

የከፍተኛ ትምሕርታቸውን በቀድሞው የቀዳማዊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተከታተሉት እደማሪያም ወደ ካናዳ ተጉዘው በሞንትሪያሉ የMcGill ዩኒቨርሲቲ የቅድመ ምረቃና የድህረ ምረቃ የሕክምና ትምሕርታቸውን በመከታተል በጠቅላላ ሃኪምነት፥ በውስጥ ደዌና በሆድ ዕቃ ልዩ ሕክምና ሞያዎች ተመርቀዋል። ከዚያምም ወደ አውሮፓ ተጉዘው በለንደኑ የትሮፒካል በሽታዎች ሕክምና እና ጤና አጠባበቅ ትምሕርት ቤት ተጨማሪ ትምሕርት ተከታትለው
በ1960ዎቹ መገባደጂያ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ፋኩሊቲ በመምሕርነት፥ የውስጥ ደዌ ሕክምና ትምሕርት ክፍል ኃላፊነት እና በኋላም በፋኩልቲው በዲንነት አገልግለዋል።

ፕሮፌሰር እደማሪያም ከውጭ አገር ተመልሰው የአዲስ አበባውን የሕክምና ትምሕርት ቤት በመምሕርነት በተቀላቀሉበት ወቅት፤ በትምሕርት ቤቱ የነበሩት የሚበዙት የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ባለሞያዎች ሲሆኑ፤ የኢትዮጵያውያኑ ሃኪሞች ቁጥር በጣም ጥቂት ነበር። በተከተሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ትምሕርት ቤቱን ማገልገል የጀመሩት ፕሮፌሰር እደማሪያም በግል ጥረታቸው የድሕረ ምረቃ የሕክምና ትምሕርት ፕሮግራሞች እንዲከፈት በትጋት መሥራታቸውን ከቀድሞ ተማሪዎቻቸው አንዱ የነበሩት በሕክምና ትምሕርት ቤቱ የቀድሞው የሳምባ ሕክምና ክፍል ኃላፊ እና አማካሪ ሃኪሙ ፕሮፌሰር ጌታቸው አደራዬ አስረድተዋል።

“ሃኪም” ማለት ምን እንደሆንና የክህነትን ያህል ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ገና የሕክምና ሳይንስ ሃሁ ቆጠራውን እንደያዙ ያስተማሩዋቸው ፕሮፌሰር እደማሪያም መሆናቸውን የሚያስረዱት ሌላው ከቀድሞ ተማሪዎቻቸው አንዱ ከዋሽንግተን ዲሲ አጎራባቿ የራክቪል የሕክምና ማዕከል የደረት፥ የጽኑ ሕሙማንና የእንቅልፍ ሁከቶች ሃኪሙ ዶ/ር አሰፋ ጄጃው ናቸው።

“በሕክምና ሞያ እጅግ የተወጣለት ሃኪም፥ ለሕመምተኛና ለተማሪ ከፍ ያለ ክብር የሚሰጡ፤ ጥሩ ተማሪ የሚያፈራና ከእርሱ የተሻሉ እንዲሆኑ የሚያደርግ፤ ተማሪ ሆነን ተሳስተሃል ብለን ደፍረን እንድናገረው የሚያበረታታን ፕሮፌሰር፤ ለሞያው የረቀቀ ክብር ያለው “ሃኪም” የሚለው መጠሪያ ለእርሱ የተጻፈ የሚመስል ባለሞያ ነበር።” ብለዋቸዋል።

ፕሮፌሰር እደማሪያም የጉበት በሽታና ሌሎች የሆድ ዕቃ በሽታዎችን ጨምሮ በአገር ውስጥ የሕክምና ምርምርና ጥናቶችን በመጀመርም በርከት ያሉ ሥራዎችን የሠሩ የሳይንስ ሰው ናቸው።

ፕሮፌሰር እደማሪያም ጸጋ፥ ከካናዳዊቱ ከያኔዋ የሕክምና ትምሕርት ቤት ጓደኛቸው ከባለቤታቸው ፍራንሲስ ጸጋ ሌስተር የወለዷቸው፤ የሦሥት ሴቶች ልጆች (አይዳ፥ ናኦሚ እና ዮዲት እደማሪያም) እንዲሁም የአንድ ወንድ ልጅ (የዮሃንስ እደማሪያም) አባት ነበሩ።

ከሁለት የቀድሞ ተማሪዎቻቸው ጋር የተካሄደውን ቃለ ምልልስ ከዚህ ያድምጡ።

ዕውቁ ኢትዮጵያዊ ሃኪም ፕሮፌሰር እደማሪያም ጸጋ ማን ነበሩ?
please wait

No media source currently available

0:00 0:09:43 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG