በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አንጋፋው የመድረክ ሰው ፍቃዱ ተክለማሪያም አረፈ


ፍቃዱ ተክለማሪያም
ፍቃዱ ተክለማሪያም

አርቲስት ፍቃዱ ተክለማሪያም ባደረበት የኩላሊት ሕመም ላለፉት በርካታ ወራት በሕክምና እና (ኋላም በጸበል ሲረዳ) ቆይቶ በትላንትናው ዕለት፤ በተወለደ በ62 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

በ1967 ዓመተ ምህረት በአዲስ አበባ የቲያትርና ባህል አዳራሽ የትወና ሞያን “ሃ” ብሎየጀመረው ፍቃዱ ተክለማሪም በ1968 ዓመተ ምህረት በሃምሌት ቴአትር ለመጀመሪያ ጊዜ በመሪ ተዋናይነት የመጫወት ዕድል ካገኘባት ከተጫወተበት ጊዜ አንስቶ የመድረክ ፈርጥ በመሆን በበርካታ ቴአትሮች ተጫውቷል።

ፍቃዱ ተክለማሪያም፤ በልዩ አጨዋወቱ ታዋቂነትን ካተረፈባቸው ምርጥ-ምርጥ ቴአትሮች መካከል ኦቴሎ፣ ቴዎድሮስ፣ መቃብር ቆፋሪው፣ የሬሣ ሳጥን ሻጩ፣ አቡጊዳ ቀይሶ፣ ባለካባ ባለዳባ፣ መልዕክተ ወዛደር፣ ኤዲፐስ ንጉሥ፣ ንጉሥ አርማህ፣ የሰርጉ ዋዜማ እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ የትወና ብቃቱን ያህል፣ ምግባርና ጠባዩን በማወደስ የሚገልጡ የሞያ ሃጋሮቹ ብዙዎች ናቸው።

የኩላሊት ከፍተኛ ቀዶ ሕክምና እንዲሚያስፈልገው ይፋ መደረጉን ተከትሎ አፋጣኝ ሕክምና ያገኝ ዘንድ፤ ሕክምናው የሚጠይቀውን የገንዘብ ወጭ እና ተተኪ ኩላሊት ለመለገስ ጭምር ቁጥሩ የበዛ ፍቃደኛ ድጋፍ ማግኘቱም በጊዜው ተዘግቧል። ፍቃዱ ከወዳጆቹና ከአድናቂዎቹ ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ 200 ሺህ ብር በተመሳሳይ ተተኪ ኩላሊት ለሚያስፈልጋት ታማሚ ወጣት መለገሱ ይታወቃል።

በመድረክ በተጫወታቸው በርካታ ቴአትሮች፤ የሬዲዮና የቴሌሺዥን ድራማዎች፤ እንዲሁም የሲኒማ ትዕይንቶች ተዋናይነት ባሳየው ልዩ የትወና ብቃቱ፣ ከፍተኛ አድናቆት እና ተወዳጅነት ያተረፈው ዕውቁ ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማሪያም ሕመሙ እሰከጠናበት ቅርብ ጊዜ ድረስ ከመድረክ አልተለየም ነበር።

ፍቃዱ በትወና ሞያው በ1994 ዓመተ ምህረት የኢትዮጵያ ሥነ ጥበባት እና መገናኛ ብዙኃን ሽልማት ድርጅት ተሸላሚ ነበር።

አንጋፋው የመድረክ ሰው ፍቃዱ ተክለማሪያም አረፈ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:28 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG