እስራኤል ኢራን የሲቪል ማመላለሻ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ለአሸባሪው ሂዝቦላህ ቡድን ገንዘብ ታቀብላለች የሚል ክስ ከአቀረበች ከአንድ ቀን በኃላ፣ ሊባኖስ ማሃን የተሰኘው የኢራን አየር መንገድ ንብረት የሆነ በረራ ወደ ቤይሩት እንዳይገባ አግዳለች።
ሊባኖስ የማረፍ ፍቃድ መከልከሏን ተከትሎም፣ የኢራኑ አየር መንገድ ወደ ቤይሩት ሊያደርገው የነበረውን በረራ አውሮፕላኑ ከመነሳቱ በፊት መሰረዙን፣ የታህራን ኢማም ኮሜይኒ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰኢድ ቻላንድሪ ለኢራን መንግሥት የዜና ወኪል ተናግረዋል።
አንድ የኢራን ጋዜጠኛ ኤክስ በተሰኘው መተግበሪያ ላይ ባጋራው እና የቪኦኤ የፋርስ ቋንቋ አገልግሎት ትክክለኛነቱን ባረጋገጠው የቪዲዮ መረጃ፣ በአውሮፕላኑ ተሳፍረው የነበሩ መንገደኞች ሲጠባበቁ እና ትእግስቱ ያለቀ አንድ ግለሰብ በመቆየቱ ተሰላችቶ ሲጮህ ያሳያል።
የሊባኖስ ሲቪል አቪዬሽን በውሳኔው ዙሪያ ከአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ አርብ እለት ለቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
ሆኖም መስሪያቤቱ ባወጣው መግለጫ፣ ሊባኖስ መካከለኛው ምስራቅ አየር መንገድ ከተሰኘው ብሔራዊ አየር መንገድ ጋር በመተባበር፣ በታህራን የሚገኙት ዜጎች ወደ ቤይሩት የሚመለሱበትን መንገድ እያመቻቸ መሆኑን ገልጿል።
ሊባኖስ ርምጃውን የወሰደችው የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ አቪቻይ አድራኤ፣ ረቡዕ ዕለት በአረብኛ በሰጡት መግለጫ፣ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጋርድ ኃይል ወደ ቤይሩት የሚበሩ የመንገደኞችን በረራ በመጠቀም ለሂዝቦላህ ገንዘብ ያዘዋውራል በማለት መክሰሳቸውን ተከትሎ ነው።
ማሃን የተሰኘው የኢራን አየር መንገድ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለሂዝቦላህ የገንዘብ እና ጦር መሳሪያ ድጋፍ ያደርጋሉ በማለት ማዕቀብ ከጣለችባቸው የኢራን ተቋማት አንዱ ነው።
መድረክ / ፎረም