በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢራን በእስራኤል ላይ የሰነዘረችውን ጥቃት ተከትሎ ግጭት እንዳይባባስ የዓለም መሪዎች ጥሪ አቀረቡ


ኢራን በእስራኤል ላይ ድሮን እና ሚሳይል ከወረወረች በኋላ፣ አራድ፣ እስራኤል፣ እአአ ሚያዝያ 14፣ 2024
ኢራን በእስራኤል ላይ ድሮን እና ሚሳይል ከወረወረች በኋላ፣ አራድ፣ እስራኤል፣ እአአ ሚያዝያ 14፣ 2024

ኢራን በእስራኤል ላይ ያካሄደችውን የድሮን እና የሚሳይል ጥቃት ተከትሎ፣ በእስራኤል እና በኢራን መካከል ያለው ሁኔታ እንዳይባባስ መንግሥታቸው የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሰኞ እለት አስታውቀዋል።

ማርኮን BFM-TV እና RMC በተሰኙት የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን ባደረጉት ንግግር እስራኤል ግጭቱን ከማባባስ ይልቅ፣ ኢራንን የማግለል አቅጣጫ እንድትከተል ጠይቀዋል።

የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾውዝ በበኩላቸው ሰኞ እለት ባስተላለፉት ተመሳሳይ መልዕክት፣ ኢራን በእስራኤል ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዳትሰነዝር አስጠንቅቀው፣ እስራኤልም ሁኔታውን በማርገብ ረገድ የራሷን ሚና እንድትጫወት ጥሪ አቅርበዋል።

የእስራኤል ባለስልጣናት የትምህርት እንቅስቃሴዎች ሰኞ መቀጠላቸውን እና በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ተጥሎ የነበረው ገደብም በአብዛኛው እንደሚነሳ አስታውቀዋል።

በኢራንም እስራኤል ላይ በተደረገው ጥቃት ምክንያት ስራቸውን አቋርጠው የነበሩ የሀገሪቱ አየር ማረፊያዎች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያቸው መመለሳቸውን የመንግስት ሚዲያዎች ገልጸዋል።

ኢራን ጥቃቱን ያካሄደችው፣ እስራኤል መጋቢት 23 ቀን ደማስቆ በሚገኘው የኢራን ቆንፅላ ጽ/ቤት ላይ ላደረገችው ጥቃት ምላሽ ለመስጠት መሆኑን አስታውቃለች። እስራኤል በበኩሏ በርካታ የኢራን ጦር ኮማንደሮችን የገደለውን ጥቃት ማድረሷን አረጋግጣ ወይም አስተባብላ መግለጫ ባትሰጥም፣ ኢራን ከኢራን ምድር የሚነሳ ምንኛውንም የአጸፋ እርምጃ እንዳትወስድ አስጠንቅቃ ነበር።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ለኢራን ጥቃት ምላሽ ለመስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመወያየት የጦር ካቢኔያቸውን ሰብስሰበው ያነጋገሩ ሲሆን፣ የካቢኔያቸው አባል ቤኒ ጋንትዝ እስራኤል ለጥቃቱ ምላሽ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።

"ጉዳዩ እንደተጠናቀቀ ሊቆጠር ይገባል" ያሉት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢራን ልዩ መልዕክተኛ በበኩላቸው፣ እስራኤል ለጥቃቱ የበቀል እርምጃ እንዳትወስድ አሳስበው፣ እስራኤል እርምጃ ከወሰደች ግን የኢራን ምላሽ ከዚህም የከፋ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG