“በምሥራቅ ባኽሙት ውጊያ ማሸነፍ አለብን” ዜሌንስኪ
በምሥራቋ ባኽሙት ከተማ ላይ የሚካሔደው ውጊያ ወሳኝ እንደኾነ ያስረዱት የዩክሬን ፕሬዚዳንት፣ “እዚያ ከተሸነፍን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሉታዊ ጫና ይመጣብናል፤ በሀገር ውስጥም አንዳንድ ዩክሬናውያን ከሩሲያ ጋራ ወደ መስማማት እንዲያዘነብሉ ሊያደርግ ይችላል፤” ሲሉ ተናገሩ፡፡
ዜሌንስኪ፣ ትላንት ማክሰኞ ለአሶስየትድ ፕሬስ በሰጡት ቃል፣ “ሩሲያ ኃይሎቿን ከሀገራችን ሙሉ በሙሉ ሳታስወጣ የሰላም ድርድር አናካሒድም፤” ብለዋል፡፡
ሩሲያ በዩክሬይን ላይ ወረራ ከከፈተች ወዲህ፣ አራት ግዛቶችን የተቆጣጠረች ሲኾን፣ አድራጎቷን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሕገ ወጥ በማለት አውግዞታል፡፡
ምዕራባውያን የዩክሬን አጋሮች ለባኽሙት ውጊያ የተጋነነ ቦታ ባይሰጡትም ዜሌንስኪ ግን፣ እዚያ ከተሸነፍን፣ በአጠቃላዩ የጦርነቱ ይዞታ ላይ ከባድ አንድምታ ይኖረዋል፤ ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኃይል ድርጅት ሓላፊ ራፋኤል ማሪያኖ ግሮሲ፣ በአውሮፓ ውስጥ ካሉት የኒውክሊየር ኃይል ማምረቻዎች ኹሉ ትልቁ የኾነውን የዩክሬይኑን የኒውክሌየር ማምረቻ ደኅንነት የሚመለከተው ሥምምነት ወደ መቋጨቱ መቃረቡን ጠቆሙ፡፡ የሩሲያ እና የዩክሬይን ባለሥልጣናት፣ በሥምምነቱ የመጨረሻ ዝርዝር ይዘት ላይ ሲስማሙ እንደሚጠናቀቅ አመልክተዋል፡፡
የዛፖሮዢያውን የኒውክሌር ኃይል ማምረቻ ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችለውን ስምምነት ለማጠናቀቅ፣ እንደገና ወደ ሩሲያ መጓዝ ሳይኖርባቸው እንደማይቀር ግሮሲ ጠቁመዋል፡፡ ለተቋሙ ቅርብ በኾኑ አካባቢዎችም፣ ውጊያው ተባብሶ መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡