በሳህል ቀጠና የእስላማዊ ነውጠኞችን እንቅስቃሴ ለማስቆም በሚል ዘመቻ ላይ የነበሩት የመጨረሻዎቹ የፈረንሣይ ወታደሮች ዛሬ ኒዤርን ለቀው መውጣታቸውን መመልከቱን እና የአገሪቱ ሠራዊትም በይፋ ማስታወቁን የኤኤፍፒ ዜና ወኪል ከኒያሜይ ዘግቧል።
ፈረንሣዮቹ ቢወጡም፣ በመቶ የሚቆጠሩ የአሜሪካ ጦር አባላት እንዲሁም በርካታ የጣሊያንና ጀርመን ወታደሮች በአገሪቱ እንደሚገኙ ዘገባው አመልክቷል።
“ዛሬ ዓርብ የፈረንሣይ ኃይሎች ለቀው የሚወጡበት ሂደት የመጨረሻና መዝጊያው ቀን ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፣ የኒጄር ሠራዊት ተወካይ ሳሊም ኢብራሂም።
ባለፈው ሐምሌ መፈንቅለ መንግስት ያካሄዱት ጄኔራሎች፣ 1ሺሕ 500 የሚሆኑ የፈረንሣይ ጦር አባላት እና አውሮፕላን አብራሪዎች፣ ከቀድሞ ቅኝ ግዛታቸው ለቀው እንዲወጡ አዘዋል።
ኒዤር፤ በሳህል ፈረንሣይ ለቃ የወጣችበት ሶስተኛ የቀድሞ ቅኝ ግዛት መሆኗ ነው። ባለፈው ዓመት ከማሊ፣ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ደግሞ ከቡርኪና ፋሶ ለቃ ወጥታለች፡፡
ሶስቱም አገራት ከአሥር ዓመታት በፊት በማሊ የጀመረውን እና በኋላም ወደ ኒዤር እና ቡርኪና ፋሶ የተስፋፋውን የእስላማዊ ነውጠኞች ጥቃት ለማስቆም በመታገል ላይ ናቸው።
በቀጠናው ባለፉት ሶስት ዓመታት በተከታታይ በተደረጉት መፈንቅለ መንግስቶች ምክንያት፣ ከፈረሣይ ጋር የነበረው ግንኙነት ሲሻክር፣ከሩሲያ ጋር ወዳጅነቱ ተሟሙቋል።
መድረክ / ፎረም