በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በላሊበላ ተራሮች ከስልጣኔ የራቀ ቆይታ


ላሊበላ ሁዳድ
ላሊበላ ሁዳድ

ላሊበላ ሁዳድ ከላሊበላ ከተማ በስተ ሰሜን ከአሽተን ማርያም በስተቀኝ ወደ አቡነ ዮሴፍ በሚወስደው መንገድ በአንድ ተራራ ላይ እየተሰራ ያለ ሎጅ ነው፡፡ ሎጁ በስድስት ሄክታር መሬት ላይ ያረፈና ከላልይበላ ከተማ ከሁለት ሰዓት የእግርና የበቅሎ ጉዞ በኋላ ይገኛል፡፡

አስገራሚና አድካሚ የተራራ ጉዞ ታልፎ የሚገኘው ላሊበላ ሁዳድ በሁለት ድንጋዮች መካከል የሚገኝ አንድ ጠባብ መግብያ ብቻ ነው ያለው፡፡ ወደ ሎጂው ከተወጣ በኋላ በሁሉም አቅጣጫ ቁልቁል የሚታየው ገደል ነው።

ተፈጥሮ አስተካክላ ያስቀመጠቻቸውን ድንጋዬች ከተለመደው ወጣ ያለ አሰራር መሰረት ተደርጐ ነው እየተሰራ ያለው፡፡ የቦታው ልምላሜ ከተራራው አናት በግራና በቀኝ የሚታየው ያከባቢው ማራኪ ገፅታ፣ ፀሃይ የመትወጣበትና የምትጠልቅበትን ሰዓታት ፍንትው አድርጐ የሚያሳይ መልኩ የተሰሩ የመመገቢያ ስፍራዎቹ አሰራሩን ለየት ያደርገዋል፡፡

የሎጂው ባለቤት አቶ መስፍን ሃ/ስላሴ ሎጁን ለመስራት 5 ሚልዮን ብር እንደመደቡና ሙሉ በሙሉ ባህላዊ እና ያከባቢያውን ገፅታ የሚያንፀባርቅ መሆኑንም ይገልፃሉ፡፡ ሙሉ በሙሉ በአከባቢው በሚገኘው ድንጋይ ሳር እና እንጨት ለዛውም በአዲስ የግንባታ ጥበብ እየተሰራ እንዳለም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአከባቢው ያለውን የውሃ እጥረት ለመፍታት ውሃ 20 ኪሎ ሜትር ርቆ ከሚገኝ አከባቢ በቧንቧ ለመሳብ እንደታቀደ ከፀሃይ ሃይል የሚገኝ ተፈጥሯዊ ሃብት ለመጠቀም መታሰቡን ይናገራሉ፡፡

አከባቢው መብራት ከሌለበትና ከጫጫታ የራቀ መሆኑ በተለይ ደግሞ መልክአ ምድራዊ አቀማመጡ ጐብኝዎች የሚወዱትና የኢኮ ቱሪዝም ባህሪ የሚፈቅደው መሆኑንም አቶ መስፍን ይገልፃሉ፡፡

ላሊበላ ሁዳድ በሚቀጥለው አመት ህዳር ወር ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡

XS
SM
MD
LG