በምሥራቅ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ በደረሱ ሦስት የተለያዩ ጥቃቶች፣ አንድ ሮማኒያዊ ቅጥረኛ ወታደር እና ሁለት የኮንጎ ወታደሮች ሲገደሉ፣ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አሰከባሪ ኀይል አባል መቁሰሉን፣ የተለያዩ ምንጮች ትላንት እሑድ አስታወቁ።
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል አንድ የጸጥታ ባለሥልጣን፣ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት፣ የግል ቅጥረኛ የኾነው ወታደር የተገደለውና ሌሎቹ ሦስቱ ደግሞ የቆሰሉት፣ ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ፣ ከጎማ በስተሰሜን 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የኮንጎ ጦር ሰፈር ላይ በደረሰ የሚሳይል ጥቃት ነው። የጥቃቱ መነሻ ግን እስከ አሁን አልተረጋገጠም።
የሰሜን ኪቭ ዋና ከተማ፣ ላለፉት ወራት፣ በስተሰሜንና በስተምዕራብ፣ በሩዋንዳ እና በኤም-23 ተዋጊዎች ተከብባ ቆይታለች። ከከተማዋ ወጣ ባሉ አካባቢዎች በየጊዜው ውጊያ የሚካሔድ ሲኾን፣ በኪጋሊ የሚደገፉት ዐማፅያን በምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል ይዞታቸውን እያሰፉ ይገኛሉ።
በጥቃቱ የሞተውና የተጎዱት ሁለቱ ወታደሮች የሮማኒያ ዜጎች መኾናቸውንና ጉዳት የደረሰበት አራተኛው ወታደር ግን የሌላ ሀገር ዜጋ መኾኑን፣ የሮማኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ትላንት እሑድ አስታውቋል። በርካታ የሮማኒያ ቴሌቭዥን ጣቢያዎችም፣ የሞተውን ተዋጊ፥ ከኮንጎ ጦር ጋራ ውል የፈጸመ “ሮማኒያዊ የቅጥር ወታደር” ሲሉ ገልጸውታል።
በሌላ በኩል፣ ከጎማ በስተሰሜን 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ 'ቡቴምቦ' በተሰኘች ስፍራ በተፈጸመ ከበባ፣ ቢያንስ ሁለት ወታደሮች መገደላቸውን፣ የአካባቢው አስተዳዳሪ ኮሎኔል አሌይን ኪዌዋ፣ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
ጥቃቱን ያደረሱት ሰዎች ማንነት ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው የገለጹት ኃላፊው፣ ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝ ጨምረው አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ ስፍራ፣ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ፣ በተልእኮ ላይ ቆይቶ ሲመለስ በነበረ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መኪና ላይ ጥቃት ያደረሱ ሲኾን፣ አንድ የሰላም አስከባሪ አባል እግሩ ላይ በጥይት መመታቱ ተገልጿል።
የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲስ፣ በግጭት እየታመሰች በምትገኘው የምሥራቅ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰሜን ኪቭ ግዛት እየተፈጸመ ያለው ጥቃት እና የዜጎች ሞት እንዲያበቃ፣ በትላንት የእሑድ ሰንበት መልእክታቸው ተማፅነው ነበር።
መድረክ / ፎረም