በሳምንቱ መገባደጃ በሄይቲ ዋና ከተማ ውስጥ በተቀሰቀሰ አሰቃቂ ሁከት 200 ሰዎች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰኞ ዕለት አስታውቋል። ግድያው የተፈፀመው አንድ የተደራጁ ወንጀለኞች ቡድን አለቃ ፖርት - ኦ- ፕሪንስ ውስጥ የሚገኙ የባዕድ አምላኪዎችን ለመግደል በማስተባበሩ መሆኑም ተገልጿል።
ግድያውን በበላይነት የመራው የወረበሎቹ ቡድን መሪ ወንድ ልጁ ለደረሰበት ህመም ተጠያቂው የእምነቱ ተከታዮች መሆናቸውን በማመኑ ግድያውን መፈፀሙንም፣ የሰላም እና ልማት ኮምቴ የተሰኘው የሲቪል ተቋም ገልጿል።
በሄይቲ የሚንቀሳቀሰው ይህ ተቋም ባወጣው መግለጫ "በልጁ ላይ ድግምት የመላክ ችሎታ አላቸው ብሎ የሚያምናቸውን አረጋውያን እና የባዕድ አምልኮ ተከታዮችን ጭካኔ የተሞላበት ቅጣት ለመቅጣት ወስኗል" ብሏል። አክሎም "የወንበዴዎቹ ቡድን ወታደሮችም ጥቃት የደርሰባቸውን ሰዎች መኖሪያ ቤት በመለየት እና መሪው ወደሚቆጣጠረው ስፍራ በመውሰድ ግድያው እንዲፈፀምባቸው ረድተዋል" ሲል አብራርቷል።
ኃያል መሆኑ በተገለጸው የወረበሎች መሪ፣ ዋና መዲናዋ ውስጥ በተቀነባበረው ግድያ ቢያንስ 184 ሰዎች መገደላቸውን ያስታወቁት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመብት ተቋም ኮሚሽነር ቮልከር ተርክ፣ "ይህ ግድያ በዚህ ዓመት ብቻ በሄይቲ ውስጥ የተገደሉትን ሰዎች ቁጥር ወደ 5ሺህ ያደርሰዋል" ብለዋል።
የተደራጁ ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር፣ በኬንያ የሚመራ የፖሊስ ድጋፍ ተልዕኮ በዩናይትድ ስቴትስ እና በመንግስታቱ ድርጅት ድጋፍ ቢሰማራም ወረበሎቹ አሁንም 80 ከመቶ የሚሆነውን የከተማዋን ክፍል እንደሚቆጣጠሩ እና የሚያደርሷቸው ጥቃቶችም እየጨመሩ መሄዳቸው ተመልክቷል።
በእነዚህ ቡድኖች ምክንያት ሄይቲ ውስጥ ከ700 ሺህ በላይ ሰዎች በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሲሆን፣ ግማሽ የሚሆኑት ህፃናት መሆናቸውን የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
መድረክ / ፎረም