ዋሺንግተን ዲሲ —
ከናይጄሪያዋ ዛምፋራ ክፍለ ሃገር የተጠለፉት ሁለት መቶ ሰባ ዘጠኝ ተማሪ ልጃገረዶች ተለቅቀው የጤና ምርመራ እየተደረገላቸው ከየቤተሰባቸው ጋር እየተቀላቀሉ መሆናቸውን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ያኩቡ ሳኒ የአንደኛዋ ተጠላፊ አባት ሲሆኑ "የልጄን ድምፅ ለመጀመሪያ ጊዜ በስልክ ስሰማ እንደገና እንደተወለድኩ ነው የቆጠርኩት" ብለዋል።
የዛምፋራ ክፍለ ሃገር የፖሊስ ኮሚሽነር አቡቱ ያሮ በበኩላቸው ጠላፊዎቹ የለቀቁዋቸው ልጃገረዶች ዛሬ ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ በመኪና ተወስደዋል ጤናማ እና ደስተኞች ናቸው ብለዋል።
ልጃገረዶቹ ሊለቀቁ የቻሉት በናይጄሪያ መንግሥት በተመራ የሰላም ሂደት አማካይነት መሆኑን ነው የፖሊስ አዛዡ ያስረዱት። ሌላውን ዝርዝር ሁኔታ በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን ብለዋል።
የተጠለፉትን ልጃገረዶች ለማስለቀቅ የተከፈለ ገንዘብ ይኖር እንደሆን በግልጽ የታወቀ ነገር የለም።
የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ የተጠለፉት ልጃገረዶች መከራ በሰላም በማክተሙ ደስ ብሎኛል ብለዋል። አያይዘውም የጦር ሰራዊቱ እና ፖሊስ ጠላፊዎቹን ማሳደዱን ይቀጥላል ካሉ በኋላ ህዝቡም መንግሥት እንዲህ ያለውን አድራጎት ለማስቆም እንዲችሉ ጥቆማ በመስጠት እንዲረዳ ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ተማጽነዋል።