በኬንያ የሚመራው የጸጥታ ተልዕኮ ኃይል ከሰኔ ወር ጀምሮ በሃይቲ ከተሰማራ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ እሑድ ዕለት፣ ከዋና ከተማው ፖርት-ኦው-ፕሪንስ በስተሰሜን በሚገኝ ስፍራ አንድ የኬንያ ፖሊስ መገደሉን የተልዕኮው ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ የፀጥታ አባላትን ያካተተው የሄይቲ የድጋፍ ተልዕኮ እሑድ እለት ባወጣው መግለጫ ኬንያዊው የፖሊስ አባል ከወንበዴዎቹ ጋራ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ላይ መቁሰሉ እና ወደ ሆስፒታል መወሰዱን፣ በኋላም ህይወቱ ማለፉን አመልክቷል።
የተልዕኮው ቃል አቀባይ ጃክ ኦምባካ ለሮይተርስ በሰጡት ቃል፣ እሁድ እለት የደረሰው ጉዳት፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚደገፈው የፀረ-ወንበዴ ኃይል ወደ ሄይቲ ከገባ ወዲህ የመጀመሪያው ነው።
"ህይወቱ ላለፈው ጀግናችን ክብር እንሰጣለን" ያለው መግለጫው "እነዚህን ወንበዴዎች እስከመጨረሻው ድረስ እንሳድዳቸዋለን። አናሳፍርህም" ሲል መልዕክት አስተላልፏል።
የኬንያው ፖሊስ ህይወት ያለፈው፣ ባለፉት ሳምንታት በሃይቲ ዋና ከተማ ፖርት-ኦው-ፕሪንስ አካባቢ በተደራጁ ወንጀለኞች የሚደርሱ ሁከቶች እየጨመሩ ባሉበት ወቅት ነው።
መድረክ / ፎረም