በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአውሮፓ ህብረት ኬንያ ለህገ መንግሥቱ ውሳኔ ህዝብ በያዘቸው ዝግጅት ደስተኛነቱን ገለጠ


የአውሮፓ ህብረት ልዑካኑ የፊታችን ረቡዕ ለሚካሄደውና ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ ለቆየው ውሳኔ ህዝብ ስለተደረገው ዝግጅት ለመረዳት ባለፈው ሰኞ ከኬንያ ጊዛዊ ነጻ የምርጫ ኮሚሽን ኣባላት ጋር ስብሰባ አድርገዋል። ሎጂስቲካዊ ዝግጅቱን እና በህገመንግስቱ ላይ ስለሚደረገው ምርጫ ህዝቡን የማስተማሪያ ፕሮግራሞች ላይ ያተኮረ ውይይት ነበር።

በኬንያ የአውሮፓ ህብረት ልዑካን መሪ አምባሳደር ኤሪክ ቫን ደር ሊንድን ኮሚሹንና ሲቪል ማህበረሰባቱን ስለጥረታቸው አድናቆት ሰጥተዋል። በሂደቱ ግልጽነት መደሰታችውንም ገልጠው ፕሬዚደንት ሙዋይ ኪባኪ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ በጉዳዩ ላይ በሚደረገው ህዝባዊ ክርክር ለተጫወቱት ሚናም አመስግነዋል።

የአውሮፓ ህብረት ልዑካኑ በተጨማሪ ከምርጫው በፊትም ሆነ በኋላ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሚኖረው ሚና ላይም ተወያይተዋል።

የጊዜያዊው ነጻ የምርጫ ኮሚሽኑ ሊቀመንበር ኢሳቅ ሃሳን ምርጫው ነጻ፣ ፍትሃዊና ግልጽ እንደሚሆን ለልዑካኑ አረጋግጠዋል። የህብረቱ ተወካዮች በናይሮቢ ድምጽ ሲቆጠር ተገኝተው እንዲታዘቡ ጋብዘናል ሲሉም የአስመራጭ ኮሚሽኑ ጊዜያዊ ሊቀመንበር ለጋዜጠኞች እስታውቀዋል።

ህዝቡ ድምጹን እንዲሰጥ ሂደቱም የሰመረ እንዲሆን እንዲያግዝ ሃሳን ተማጽነዋል።

ፕሬዚደንት ኪባኪ ህዝቡ በብዛት ወጥቶ ድምጹን እንዲሰጥ ዕለቱን ብሔራዊ በዓል አድርገው እንዲያውጁት ኮሚሽኑ መጠየቁንም ሊቀመንበሩ ተናገረዋል። ፕሬዚደንቱ ገና መልስ አልሰጡበትም ነገር ግን ተፈጻሚ እንደሚያደርጉት እተማመናለሁ ብለዋል ።

የፊታችን ረቡዕ የሚካሄደው ውሳኔ ህዝብ ውጤት ምንም ይሁን ምን የብሔራዊ አንድነት መንግስቱን ታሪክ የሚወስን መሆኑ ግን አይቀርም ።

ፕሬዚደንት ሙዋይ ኪባኪና ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ የሰላም ውል ሲፈራረሙ
ፕሬዚደንት ሙዋይ ኪባኪና ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ የሰላም ውል ሲፈራረሙ

ጥምር መንግሥቱ የተቋቋመው እኤአ ከታህሳስ 2007 አጨቃጫቂ ምርጫ በኋላ ፕሬዚደንት ሙዋይ ኪባኪና ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ በተፈራረሙት የሰላም ውል ነው።

በሁለቱም ወገኖች የምርጫ መጭበርበር ንትርክ መላ ሀገሪቱን ሁለት ወር ሙሉ በብሔረሰብ ሁከት ከአንድ ሺህ የሚበልጥ ህዝብ መገደሉና ሶስት መቶ ሺህ የሚጠጋ ከቤት ንብረቱ መፈናቀሉ ይታወሳል። ረቡዕ የተካሄደው የህገ መንግስቱ ምርጫ ሂደትም ያን ሁከት ያቆመው የሰላም ውል አካል ነው። በቅርቡ የተካሄደ የህዝብ አስተያየት ግምገማ እንደሚያሳያው ከህዝቡ ስድሳ ከመቶው የረቀቀውን ህገ መንግስት ይደግፋል።

XS
SM
MD
LG