የኬንያ ፖሊስ በቅርቡ የአገሪቱ ፓርላማ ያረቀቀውን መጠነ ሰፊ የግብር ጭማሪ የሚጠይቅ ረቂቅ የፋይናንስ ሕግ ለመቃወም በወጡ ሰልፈኞች ላይ አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል።
ሰልፈኞቹ ወደ ፓርላማ እንዳይገቡ ለማድረግ ቁጥሩ የበዛ ፖሊስ ተሰማርቷል።
የኬንያ መንግስት ሃገሪቱ ያለባትን ግዙፍ ዓለም አቀፍ ዕዳ ወለድ ክፍያ ለመቀጠል ያስፈልገኛል በሚል ያቀረበውን ረቂቅ ሕግ በመቃወም ከቅርብ ቀናት ወዲህ በወጣቶች የሚመራ የማኅበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ በኬንያ እየጨመረ መምጣቱ ተመልክቷል።
በአንጻሩ የተቃውሞ ሰልፎቹ በአብዛኛው ሰላማዊ መሆናቸው ቢዘገብም፤ ባለፈው ሳምንት በተካሄዱ መሰል የተቃውሞ ሰልፎች ወቅት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን ያመለከቱ አንዳንድ የሃገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ “ፖሊስ በሕገ ወጥ መንገድ ሰልፈኞችን እያሰረ ነው” ሲሉ ከሰዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሕግ አውጭዎች ቀደም ሲል በረቂቅ ሕጉ ተካተው የነበሩ በዳቦ፣ በተሽከርካሪዎች ባለቤትነት እና በግብይት ልውውጥ ላይ ሊጣሉ የታቀዱ አንዳንድ የቀረጥ ጭማሪዎችን ሰርዘዋል። የገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ በረቂቅ ሕጉ ላይ የሚደረግ ለውጥ የ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የበጀት እጥረት ይፈጥራል ብሏል።
በዛሬው ዕለት በደቡብ ምስራቅ የወደብ ከተማይቱ ሞምባሳ እና በምዕራባዊቱ የኪሱሙ ከተማ ረቂቅ የፋይናንስ ሕጉን በመቃወም ሰልፎች መካሄዳቸው ታውቋል።