የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በኬንያ እያካሔደው ነው የተባለውን ሕገወጥ እንቅስቃሴ እና ወንጀሎች ለማስቆም፣ የኬንያ ፖሊስ በድንበሩ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የሰራዊቱ አባላት ላይ ርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትም ከኬንያ መንግሥት ጋራ ተቀናጅቶ በሰራዊቱ ላይ ርምጃ መውሰድ መጀመሩን አረጋግጧል። የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በበኩሉ አባላቱ ፈፀሙ የተባሉትን ወንጀል እንደማይፈፅሙ ገልፆ፣ በወንጀል ትስስሮች ውስጥ ተሳታፊ ሆነው ከተገኙ ግን ርምጃ ለመውሰድ ቃል ገብቷል።
የኬንያ ፖሊስ፣ በማርሳቢት እና ኢሲኦሎ አውራጃዎች በሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ታጣቂዎች ላይ ያነጣጠረ የጸጥታ ርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታውቋል።
የኬንያ ፖሊስ ጉዳዩን አስመልክቶ በአወጣው መግለጫ፣ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት "በኬንያ ብሔራዊ ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ስጋት የደቀኑ የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ ተሳትፎ አለው" ሲል ከሷል።
ወታደራዊ ዘመቻው ለአንድ ወር ያክል ሲካሄድ መቆየቱን ያመለከተው የኬንያ ብሔራዊ ፖሊስ አገልግሎት፣ እስካሁን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አባላቶች በቁጥጥር ስር ስለመዋላቸው አላስታወቀም።
የኬንያ ብሔራዊ ፖሊስ ዋና ዳይሬክተር ዳግላስ ካንጆ ኪሮቾ በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ የኬንያ ፖሊስ በኬንያው ኢሲዮሎ እና የኢትዮጵያ ሞያሌ ከተሞች መካከል የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ላይ ያነጣጠረውን ወታደራዊ ዘመቻ የጀመረው እ.አ.አ ጥር 3፣ 2025 መሆኑን ተናግረዋል።
"የኦሮሞ ነፃነት ጦር በኬንያ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ሕገወጥ የጦር መሳሪያ እና አደንዛዥ እፅ ዝውውር፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የኮንትሮባንድ እቃዎች ንግድ፣ ድንበር ተሻጋሪ ወረራዎችን ማድረግ፣ ሕገወጥ የማዕድን ቁፋሮ፣ የጎሳ ግጭቶችን መፍጠር እና ገንዘብ ለማግኘት የሚደረግ እገታን እንደሚያካትት እና ይህም በኬንያ ብሔራዊ ደህንነት ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀኑን ተናግረዋል።"
ዋና ዳይሬክተሩ አክለው፣ ጦሩ ኬንያ በሚገኘው የቦረና ማኅበረሰብ እና በኢትዮጵያ በሚገኘው የኦሮሞ ማኅበረሰብ መካከል ያለውን ቤተሰባዊ የባህል ትስስር በመጠቀም በማርሳቢት እና ኢሲኦሎ አውራጃዎች በሚኖረው ኅብረተሰብ መካከል ሰርጎ መግባት እና መደበቅ መቻሉን አብራርተዋል።
አክለውም፣ "በማርሳቢት እና ኢሲኦሎ አውራጃ ውስጥ በሕዝብ መካከል ሰርጎ በመግባት እና እና በመደበቅ፣ በኬንያ እና በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ በሚኖሩ ማህበረሰቦች ላይ አሰቃቂ ግድያ ይፈፅማሉ፣ የሰዎችን ንብረት በግዳጅ ይነጥቃሉ፣ በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይም ጾታዊ ጥቃትን ይፈፅማሉ።" ብለዋል።
በኬንያ እየተካሄደ ያለውን ወታደራዊ ኦፕሬሽን አስመልክቶ የኢትዮጵያ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ ሸኔ ሲል የሚጠራው የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ፣ የሰዎችና የማዕድን ንግድ እንዲሁም የጎሳ ግጭት በመቀስቀስ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የሀገሪቱ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት ሆኖ መቆየቱን አስታውቋል። ከኬንያ የደኅንነትና የጸጥታ ተቋማት ጋራ በመሆንም በታጣቂዎቹ ላይ የተቀናጀ ዘመቻ ማካሄድ መጀመራቸውን አረጋግጧል።
የደኅንነት አገልግሎቱ ለሀገር ውስጥ የዜና አገልግሎት ለሆነ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) በላከው መረጃ፤ የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የኬንያ ብሔራዊ መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ኑረዲን ሞሐመድ ሐጂ እንዲሁም የሁለቱ ሀገራት የመከላከያ እና የፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች ምክክር ማድረጋቸውን አመልክቶ፣ የሁለቱ ሀገራት የደኅንነትና የጸጥታ አካላትም በየድንበራቸው ውስጥ በሚገኙ የቡድኑ ካምፖች ላይ የተቀናጀ ኦፕሬሽኖች እያካሄዱ ይገኛሉ ብሏል፡፡
የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በኬንያ በኩል የቀረቡበትን ውንጀላዎች እና በአባላቱ ላይ የሚካሄደውን ዘመቻ አስመልክቶ ዛሬ ማክሰኞ ጥር 27፣ 2017 ዓ.ም በሰጠው ምላሽ፣ "ሉዓላዊነትን እና የግዛት አንድነትን እንደሚያከብር" እና ማንኛውንም አይነት የወንጀል ድርጊት እንደሚቃወም አመልክቶ ድንበር ላይ ያሉ ወንጀሎችን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ከኬንያ ባለስልጣናት ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ መሆኑን ገልጿል።
ኖርዌይ እንደሚገኙ እና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አማካሪ መሆናቸውን የገለጹት ጂረኛ ጉደታ በአሜሪካ ድምፅ የኦሮምኛ ቋንቋ ክፍል ተጠይቀው በሰጡት ምላሽም፣ ሰራዊቱ በአብዛኛው በኦሮሚያ ክልል እንደሚንቀሳቀስ እና በኬንያ ድንበር ውስጥ የሚገኘው አባል ብዛት ጥቂት መሆኑን አመልክተው፣ ፈፀሙ የተባሉትን ወንጀሎች ግን እንደማይፈፅሙ በመግለጽ አስተባበለዋል።
እንደዚህ አይነት ወንጀሎችን መስራት በሰራዊቱ ሕገ ደንብ ከባድ ቅጣት እንደሚያስቀጣ ያመለከቱት አቶ ጂረኛ፣ ሕገወጥ ድርጊቶቹ ከምርጫቸው ተለይተው መፍትሄ ካልተሰጣቸው በድንበር ላይ ብቻ በሚደረግ ዘመቻ የሚቆም አይደለም ባለመሆኑ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጠይቀዋል።
አቶ ጂረኛ አክለው ሰራዊቱ በኬንያ ድንበር አካባቢ በሚገኙ ጫካዎች ውስጥ የከባድ መሳሪያ ተኩስ ከመስማታቸው ባለፈ በሰራዊቱ ላይ እርምጃ ስለመወሰዱም ሆነ በአባሎቻቸው ጉዳት ስለመድረሱ አለመስማታቸውን ተናግረዋል።
የሰራዊቱ መግለጫ አክሎ "የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት ለቦረና እና ለሌሎች የኬንያ ማህበረሰቦች ደህንነት እና ጸጥታ ያለው ቁርጠኝነት የጸና ነው። ሰላማዊ ህልውናቸውን የሚያውክ ማንኛውንም አይነት የወንጀል ድርጊት እንቃወማለን" ያለ ሲሆን፣ አባላቱ በአገር አቀፍ የወንጀል ትስስሮች ውስጥ ተሳታፊ ሆነው ከተገኙ ርምጃ ለመውሰድ ቃል ገብቷል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃ እና ደህነንት አገልግሎት በመግለጫው፣ መጠነ ሰፊ ሲል የገለጸው እና ኬንያ እና ኢትዮጵያ በየድንበራቸው የሚያካሂዱት የተቀናጀ ወታደራዊ ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክቶ "የሸኔ ታጣቂ ቡድን የቀረበለትን የሰላም ጥሪ በመርገጥ በራሱ ላይ ጥፋት ቢያውጅም፤ አሁንም የሰላም መንገዱ ዝግ አይደለም" ብሏል።
ዘመቻው እየተካሄደ ያለው ኬንያ እና ኢትዮጵያ በጋራ ባካሄዱት መድረክ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ቀጣናዊ የጸጥታ እና ደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የተፈራረሟቸውን ስምምነቶች መሠረት መሆኑን አመልክቷል።
የኬንያ ፖሊስ በበኩሉ፣ የአካባቢውን ሰላም ለመመለስ እና የሁሉንም ኬንያዊ ህይወት እና ንብረት ለመጠበቅ የሚያስችል ሕግ የማስከበር ስራ እየሰራ ባለበት ወቅት ነዋሪዎች እንዲረጋጉ፣ ከፀጥታ አባላት ጋር እንዲተባበሩ እና የእለት ተእለት ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ አሳስቧል።
የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት፣ የኦሮሞ ሕዝብ መገለል እንደደረሰበት በመግለጽ እ.አ.አ ከ2019 ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጦር ጋር እየተዋጋ ይገኛል። ከኦሮሞ ብሔረሰብ የሚወለዱት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን የመጡት እ.አ.አ በ2018 ነበር።
መድረክ / ፎረም