በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኬንያ መንግሥት አንዳንድ የግብር እርምጃዎችን ወደነበሩበት ሊመልስ ነው


ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ
ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ

የኬንያ መንግስት በቅርቡ በተቀሰቀሰው ተቃውሞና ሁከት ሳቢያ አስቀርቷቸው ከነበሩት የግብር (ታክስ) ህጎች ውስጥ አንዳንዶቹን መልሶ ተግባራዊ በማድረግ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለመሰብሰብ ማቀዱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አስታወቁ፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ ጆን ምባዲ ትላንት እሁድ ሲቲዝን ቲቪ ለተባለ አንድ የግል ቴሌቭዥን ጣቢያ እንደተናገሩት መንግስት ወደ 150 ቢሊዮን ሽልንግ (1.2 ቢሊዮን ዶላር) ለመሰብሰብ እንዲችል ወደ 49 የሚጠጉ የታክስ እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እያሰበ ነው ብለዋል።

ከእነዚህ መካከል እንደ ኤሌክትሮኒክስ እቃዎችና መንግስት እላቂና ውዳቂዎችን ለመቀነስ ይረዳሉ ያላቸውን እንደ የፕላስቲክ ማሸጊያዎች የመሳሰሉትን እቃዎች ያካታታል ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ባለፈው ሰኔ በናይሮቢ ደም አፋስሽ በነበረው ሁከት መንግሥታቸው አወዛጋቢውን የታክስ ህግ ማስቀሩትን በተናገሩበት ወቅት መንግሥት የበጀት እጥረት እንደሚገጥመው አስጠንቅቀው ነበር፡፡

ሩቶ ወደ 2.7 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ከግብር ለመሰብሰብ ያቀዱበትን የእኤአ የ2024 ፋይናንስ ህጋቸውን ከሰረዙ በኋላ ክፍተቱን ለመድፈን የመንግሥት ወጭ እንደሚቀንስ እና የብድር መጠንን እንደሚጨምር አስታውቀዋል፡፡

በግብር ማሻሻያ ህግ ውስጥ የተካተቱት አዳዲስ እርምጃዎች በመስከረም መጨረሻ ላይ ተግባራዊ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡

እኤአ የ2024 የፋያናንስ ህግ መቅረት፣ የመንግሥትን ያለበትን የ78 ቢሊዮን ዶላር እዳ መክፈል ብቃት ስጋት ውስጥ ከትቶታል፡፡ በዚህ የተነሳም የተበዳሪዎችን ደረጃ የሚያወጡት ዓለም አቀፍ የሞዲ እና ፊች ተቋማት የኬንያን ደረጃ ዝቅ አድርገውታል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG