ኬኒያ ውስጥ 47 ሰዎች “በጾም ራሳችሁን አስርባችሁ ብትሞቱ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ትገናኛላችሁ” ያሏቸውን የሃይማኖት መሪያቸውን ተከትለው በረሃብ መሞታቸውን የሀገሪቱ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ማሊንዲ በምትባል ከተማ በሚገኝ የሃይማኖት መሪው ንብረት በሆነ መሬት ላይ የተቀበሩ 26 ተጨማሪ አስከሬኖች ትናንት ዕሁድ ለፍለጋ በተሰማሩ ሰራተኞች መገኘታቸውን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የመልካም ዜና ዐለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን መሪው ፖል ማኬንዚ ኢንቴንጌ ምዕመናኑን “በረሃብ ብትሞቱ እየሱሱን ታገኙታላችሁ” ያሏቸው ሲሆን አንዳንዶቹ አእምነዋቸው የተባሉትን አንዳደረጉ ተመልክቷል፡፡
የቤተ ክርስቲያኑ መሪ መሬት ላይ ተጨማሪ ሰለባዎች አሉ የሚል ጥቆማ ያገኘው ፖሊስ ሥፍራውን ወርሮ ባደረገው ፍለጋ በረሃብ ሰውነታቸው ያለቀ 15 ሰዎች እንዳገኘ እና ከመካከላቸው አራቱ ከዚያ ወዲህ እንደሞቱ አስታውቋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኑ መሪ ታስረዋል፡፡ ፖሊሶች እንዳያገኟቸው የተደበቁ ምዕመናን ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ሥጋት እንዳለ ባለሥልጣናቱ ገልጸዋል፡፡