በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የወጣቷ ሞዴልና የማስታወቂያ ባለሞያ አሟሟት በመጣራት ላይ መኾኑን ፖሊስ አስታወቀ


ትላንት መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ሕይወቷ ያለፈው ሞዴልና የማስታወቂያ ባለሞያ ቀነኒ አዱኛ።
ትላንት መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ሕይወቷ ያለፈው ሞዴልና የማስታወቂያ ባለሞያ ቀነኒ አዱኛ።

ትላንት መጋቢት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. በድንገት ሕይወቷ ያለፈው ሞዴልና የማስታወቂያ ባለሞያ ቀነኒ አዱኛ አሟሟት እየተጣራ መኾኑን ፖሊስ ጠቆመ

በኦሮምኛ ቋንቋ ዘፈኑ የሚታወቀው አንዷለም ጎሳ የፍቅር አጋር እና ሞዴልና የማስታወቂያ ባለሞያ ቀነኒ አዱኛ፣ ትላንት ሌሊት በአዲስ አበባ ከተማ ፣ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው በድንገት ሕይወቷ ማለፉን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉና ለቤተሰብ ቅርብ የኾኑ ምንጮች ተናገሩ።

ምስራቅ ሐረርጌ ውስጥ የተወለደችው ቀነኒ እና ድምፃዊ አንዷለም መኖሪያ ቤታቸው ህንጻ ላይ እንደሚገኝና፣ "ከአምስተኛ ፎቅ ራሷን ወርውራ" ሕይወቷ ማለፉን እኚኽ ለቤተሰቡ ቅርብ የኾኑ ምንጭ ገልጸዋል። ነገር ግን አሟሟቷን በተመለከተ ቪኦኤ ከፖሊስም ኾነ ለሌላ ገለልተኛ ምንጭ አላረጋገጠም።

የባህላዊ አልባሳትን በመልበስ በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በይበልጥ የምትታወቀው ቀነኒ፣ ከታዋቂው አንዷለም ጎሳ ጋራ ለሦስት ዓመታት በአንድ ቤት ይኖሩ የነበሩ የፍቅር አጋር መኾናቸውን እኚኹ ግለሰብ ነግረውናል።

አርቲስት አንዷለምን ፖሊስ ለጥያቄ ፈልጎ እንደወሰደውና ይኽ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ፣ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ ምንጫችን ነግረውናል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን፣ የጠየቅናቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ፣ በጉዳዩ ላይ መረጃ ለመስጠት ጊዜው ገና መኾኑን ተናግረዋል።

ማምሻውን ያገኘናቸው አንድ የአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ባልደረባ፣ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እያደረገ መኾኑን ከመግለጽ ውጭ ምንም መረጃ እንደማይሰጡን ነግረውናል።

የወጣት ቀነኒ አዱኛ አስከሬን ዛሬ ጠዋት ዳግማዊ በሚኒልክ ሆስፒታል የአስከሬን ምርመራ ከተደረገለት በኋላ ዛሬ ከሰዓት፣ 9 ሰዓት አካባቢ ሱሉልታ ወደሚገኘው እህቷ ቤት እንደተወሰደ ምንጩ ለቪኦኤ ተናግረዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG