በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአዲስ አበባ ግንባታና ማህበራዊ ስንክሳሩ


ከእስጤፋኖስ ቤተክርስቲያን በስተጀርባ የፈረሱ ቤቶች
ከእስጤፋኖስ ቤተክርስቲያን በስተጀርባ የፈረሱ ቤቶች

አዲስ አበባ ፈርሳ እየተገነባች ነው። ለዘመናት የማይነቃነቁ የሚመስሉት አፈርማ ቀለም ያላቸው የቆርቆሮ ቤቶች በልደታ፣ በካሳንችስ፣ በአራት ኪሎ አካባቢና በሌሎችም ያረጁ የአዲስ አበባ አካባቢዎች እየፈረሱ ናቸው።

በምትካቸው ረጃጅም ህንጻዎች ለሆቴል፣ ለቢሮና ለሌሎች አገልግሎቶች ይገነባሉ።

እነዚህ ግንባታዎች የከተማዋን ገጽታ እየቀየሩ ቢሆንም፤ ለረጂም ጊዜ የኖሩበትንና ያደጉበትን ሰፈል ለሚለቁ ቤተሰቦች ግን አስቸጋሪ ሁኔታን ፈጥሯል።

አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የከሳንችስ ነዋሪ ኢትዮጵያም ሆነች አዲስ አበባ ማደጋቸውን እንደሚፈልግ ይናገራል። በዚህ ሳቢያ ግን በርካታ ቤተሰቦች ከኑሯቸውና ከቤታቸው መፈናቀላቸው ሊታይ ይገባል ሲል ያሳስባል።

ቤተሰቦቹ የመንግስት ሰራተኞች መሆናቸውን የሚናገረው ወጣት በተለዋጭ የተሰጣቸው ቦታ ከከተማዋ በየቀኑ የ20 ብር የመጓጓዣ ወጭ የሚያስወጣ ይሆናል ይላል።

ከገንዘቡ በላይ መንገላታት አለ ስለዚህ “እናቴ ከዚያ እዚህ ድረስ መጥታ ለመስራት አቅሙም አይኖራትም። ወጭውም አይኖራትም እና ብዙ ስለሆንን ቤተሰብም ስለማይሸፍንልን የግድ ታቆማለች። እዚያ ሰፈር ስንሄድ ምን አይነት ሰው እንደምንሆን አላውቅም” ብሏል።

የልማት ስራዎቹ በርካታ ቤተሰቦችን ከሚኖሩበት ስፍራ አፈናቅለዋል፤ እያፈናቀሉም ይገኛሉ።

አቶ ካሳ ወልደሰንበት የአዲስ አበባ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽ/ቤት ቃል-አቀባይ ሰዎች ከለመዱት ስፍራ ሲነሱ ቅር መሰኘታቸው ያለ ነው ይላሉ።

“ሼራተን ሲሰራ ሰዎች ተነስተው ሲ.ኤም.ሲ ሲሄዱ ከከተማ አውጥተው ጣሉን የሚሉ ሰዎች ነበሩ። ዛሬ አንደኛ ቦታ ነው” ይላሉ አቶ ካሳ።

የሶስት ልጆች እናት የሆነች በእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ጀርባ የምትኖር ሴት ገላን ወደሚባለው አዲሱ ሰፈር የምትገባ ከሆነ፤ የልጆቿ ትምህርት እንደሚቋረጥ ትናገራለች።

በግንባታዎቹ ሳቢያ ወደ ሌላ ስፍራ የሚነሱ ሰዎች በተሰሩ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው አቅሙ ኖሯቸው 20 ከመቶ የቤቱን ዋጋ መክፈል ከቻሉ፤ እንደ አንደኛ አማራጭ ተቀምጧል ይላሉ አቶ ካሳ ወልደሰንበት።

አቅሙ ከሌላቸው ሌላ የቀበሌ ቤት እደሚሰጣቸውና የግል ቤት ያላቸው ካሳ እንደሚከፈላቸው ቃል-አቀባዩ ተናግረዋል።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG