በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የካዛክስታን ፕሬዚዳንት “ያለምንም ማስጠንቀቂያ ተኩሶ መግደል እንዲቻል” ፈቀዱ


ለሳምንት የዘለቀው የተቃውሞ አመጽ በካዛክስታን
ለሳምንት የዘለቀው የተቃውሞ አመጽ በካዛክስታን

ለሳምንት በዘለቀው የተቃውሞ አመጽ ውስጥ የምትገኘው ካዛክስታን ፕሬዚዳንት ዛሬ ለህዝባቸው ባደረጉት የቴሌቭዥን ንግግር "የጸጥታ ኃይሎች ጸረ መንግሥት ተቃዋሚዎችን ያለምንም ማስጠንቀቂያ ተኩሰው እንዲገድሉ" የሚያስችል ሥልጣን ለጸጥታ ኃይሎች መስጠታቸውን አስታወቁ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ካሲም ጆማርት ቶካዬቭ ወንጀለኞችና ነፍሰ ገዳዮች ናቸው ካሏቸው ተቃዋሚዎች ጋር መደራደር “ደደብነት” ነው ብለዋል፡፡

ራሳቸው የፖሊስነትን ሥልጣን ተቀብለው መረከባቸው የተነገረው ፕሬዚዳንቱ፣ በስም ለይተው ባልጠቀሷቸው የውጭ ኃይሎች ይደገፋሉ ያሏቸው ተቃዋሚዎችን በሽብርተኝነት በመክሰስ ብርቱ እምርጃ እንደሚወስዱ በመዛት እንዲህ ብለዋል፡

“በርግጥ እነዚህ አሸባሪ ቡድኖች አለም አቀፋዊ መሆናቸውን ማጤን አለብን። በከፍተኛ ደረጃ ሥልጠናዎችን ወስደዋል፡፡ ካዛክስታን ላይ ያደረሷቸው ጥቃቶች እንደ ጠብ አጫሪነት ድርጊት ሊወሰዱ ወይም መወሰድ ይገባቸዋል."

ፕሬዚዳንቱ የሩሲያ ሰላም አስከባሪ ኃይሎች የአገሪቱን ሰላም ለማስጠበቅ እሳቸው ባቀረቡላቸው ጥያቄ መሰረት ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

የካዛክ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ 26 የታጠቁ ወንጀለኞች የተደመሰሱ ሲሆን፣ ከ3ሺ በላይ የሚሆኑት ደግሞ መታሰራቸውን ገልጸዋል፡፡

ተቃውሞ ከተጀመረ በኋላ እስካሁን 18 ፖሊሶችና የብሄራዊ ዘብ አባላት መገደላቸው ተመልክቷል፡፡

ባለፈው ሳምንት የተቀሰቀሰው ተቃውሞ የተነሳው በአገሪቱ ም ዕራባዊ ክፍል በ እጥፍ የጨመረውን የነዳጅ ዋጋ በመቃወም መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የሩሲያው ወታደሮች ትናንት ወደ ካዛክስታን የገቡ መሆናቸው ሲገልጽ ዩናይትድ ስቴትስ ሩሲያውያኑ የአገሪቱን ተቋማት እንዳይቆጣጠሩ አሳስበለች፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊነክን ከካዛክስታን የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ጋር ትናንት በስልክ ተገናኝተው መነጋገራቸው ተዘግቧል፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ በካዛክስታን ህገመንግሥቱና የሚዲያ ነጻነት እንዲከበር አሳስባለች፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስም ትናንት በሰጡት መግለጫ የሚፈጸመውን ሰብዓዊ መብት ጥሰት ዩናይትድ ስቴትስና ዓለም በግልጽ እየተመለከቱት ነው ብለዋል፡፡

XS
SM
MD
LG