የሶማሊያ ወታደሮች በከፊል ራስ ገዝ ከሆነችው ከጁባላንድ ኃይሎች ጋራ ትላንት ከተጋጩ በኋላ ከያዙት ሥፍራ ለቀው ማፈግፈጋቸውን ሞቃዲሾ ዛሬ ሐሙስ አስታውቃለች፡፡
ግጭት የማይለያት ሶማሊያ በአምስት ከፊል ራስ ገዝ በሆኑ ክልሎች ማለትም፣ ፑንትላንድ፣ ጁባላንድ፣ ጋልሙዱግ፣ ሂርሸበሌ፣ እና ደቡብ ምዕራብ በተሰኙ ክልሎች የተዋቀረች ናት፡፡
በአህመድ ማዶቤ የሚመሩት የጁባላንድ ኃይሎች ራስ ካምቦኒ በተባለ ሥፍራ ትላንት ረቡዕ ለበርካታ ሰዓታት ከፌዴራል መንግሥት ኃይሎች ጋር ተታኩሰው እንደነበር የመንግሥት እና ወታደራዊ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
“የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት የሶማሊያውያን፣ በተለይም የሃገሪቱ ጦር ሠራዊት ደም እንዳይፈስ መከላከል ግዴታው ነው፣ በመሆኑም ሠራዊቱ ከታችኛው ጁባ ለቆ እንዲወጣ ታዟል” ሲል መንግሥት ባወጣው መግለጫው አስታውቋል። መግለጫው ዝርዝር ጉዳዮችን አላነሳም። ለግጭቱ የማዶቤን ኃይሎች ተጠያቂ አድርጓል።
ሠራዊቱ ከአል ሻባብ ኃይሎች ውጪ የትጥቅ ግጭት እንዲያደርግ መመሪያ አልተሰጠውም ሲል አክሏል መግለጫው።
ማዶቤ ባለፈው ጥቅምት የተደረገውን የሃገሪቱን ብሔራዊ የምክክር ም/ቤት ጉባኤ ረግጠው ከወጡና ምርጫ በማካሄድ የጁባላንድ ፕሬዝደንት ሆነው በድጋሚ ከተመረጡ በኋላ በሁለቱ ወገኖች በኩል ውጥረቱ ተባብሷል።
ስብሰባው የፌዴራል መንግሥት እና አንዳንድ ግዛቶች በመጪው ሰኔ 2017 የአካባቢ ምርጫ ለማካሄድ፣ በመስከረም ደግሞ የግዛቶች እና የፓርላማ ምርጫ ለማድረግ ስምምነት ላይ ቢደርስም፣ ማዶቤ ግን በተጠቀሰው ወቅት ምርጫ ለማካሄድ የሥልጣን ዘመንን ማራዘም ይጠይቃል በሚል ተቃውመው ነበር።
መድረክ / ፎረም