በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከባይደን ጋር የተወያዩት የዮርዳኖሱ ንጉስ ለጋዛ የዘላቂ የተኩስ አቁም ጥሪ አሰሙ


የዮርዳኖሱ ንጉስ አብዱላህ 2ተኛ፣ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣ ኋይት ሃውስ፣ ዋሺንግተን ዲሲ፤ እአአ 12/2024
የዮርዳኖሱ ንጉስ አብዱላህ 2ተኛ፣ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣ ኋይት ሃውስ፣ ዋሺንግተን ዲሲ፤ እአአ 12/2024

የዮርዳኖሱ ንጉስ አብዱላህ 2ተኛ ለስድስት ሳምንታት የሚዘልቅ የተኩስ አቁም ጥሪ እያሰሙ ካሉት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ነው በጋዛ እየተካሄደ ላለው ጦርነት ማብቂያ ሙሉ የተኩስ አቁም የሚጠይቀውን ጥሪያቸውን ያሰሙት።

ንጉስ አብዱላህ በተገኙበት በዋይት ሃውስ የተናገሩት ፕሬዝዳንት ባይደን በበኩላቸው ‘እስራኤል እግረኛ ጦሯን ልታሰማራ እየተዘጋጀች ባለችበት በደቡባዊ የራፋህ ከተማ ያሉ ሲቪሎች ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል’ ብለዋል። የ81 ዓመቱ ባይደን የታጋቾችን መለቀቅ ያካተተ እና ሠፊ ይዘት ያለው፣ ቢያንስ ለስድስት ሳምንታት የሚዘልቅ፡ የተኩስ አቁም በሚደረስበት ሁኔታ ላይ አገራቸው እየሰራች መሆኗን ጠቁመዋል።

የዮርዳኖሱ ንጉስ በበኩላቸው ‘እስራኤል የራፋውን ወታደራዊ ዘመቻ ጨርሶ መጀመር የለባትም’ ሲሉ ነው ያሳሰቡት። "አሁን ዘላቂ የተኩስ አቁም ውል ነው የሚያስፈልገን። ይሄ ጦርነት ማብቃት አለበት፡" ያሉት ንጉስ አብዱላህ፤ ሃማስ ባለፈው መስከረም 26 እስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የተጀመረውን ጦርነት ለማስቆም ሙሉ የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ደጋግመው ሲወተውቱ ቆይተዋል።

ከዚያ ጥቃት በኋላ ከባይደን ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው ሲነጋገሩ የመጀመሪያቸው በሆነው በዚህ ውይይትም የዮርዳኖሱ ንጉስ፡ "ሌላ ሰብአዊ እልቂት ማስከተሉ የማያጠያይቅ ነው” ያሉትን የእስራኤል የራፋህ ወታደራዊ ዘመቻ “ዝም ብለን ቆመን እያየን እንዲቀጥል ማድረግ አንችልም" ሲሉ በአጽኖት ስጋታቸውን ገልጠዋል።

‘ሙሉ የተኩስ አቁም’ ጥሪ የማቅረቡን ሃሳብ በተደጋጋሚ ሳትቀበል የቀረችው እና እስራኤልን የምትደግፈው ዩናይትድ ስቴትስ በአንጻሩ ታጋቾች ሊለቀቁ የሚችሉበት የአጭር ጊዜ ዘለቄታ ያለው የተኩስ አቁም ስምምነት ጥሪ ስታሰማ ቆይታለች። ሆኖም ባይደን ባለፈው ሳምንት እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ያለውን ወታደራዊ ምላሽ "ከሚገባው በላይ” ሲሉ ቁልፍ አጋራቸው በሆነችው እስራኤል ላይ ጠንከር ያለ አቋም ሲይዙ ታይተዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG