በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ኩባኒያ የተሰራው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ጉዳይ


የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የጤና ባለሥልጣናት በጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ኩባኒያ በተሰራው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ላይ ተጨማሪ ክትትል በማድረግ ላይ ናቸው።

የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ሲዲሲ ዳይሬክተር ዶ/ር ሮሼል ዋሌንስኪ ትናንት ሰኞ በዋይት ሃውስ በሰጡት ቃል ባንድ ጊዜ ከሚሰጠው ክትባት ጋር ተያያዥ ሊሆኑ የሚችሉ የጎንዮሽ የጤና ዕክሎች የገጠሙዋቸው ተጨማሪ ተከታቢዎች አሉ የሚሉ ሪፖርቶችን እየተከታተልን ነን ብለዋል።

"ቁጥራቸው ብዙ አለመሆኑ የሚያበረታታ ነው ቢሆንም እነሱኑ የተገኙትን እየተከታተልን ነን" ሲሉም የሲዲሲዋ ዳይሬክተር አክለው ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ዕድሜያቸው ከአስራ ስምንት እስከ አርባ ስምንት ዓመት በሆኑ ስድስት ሴቶች ላይ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰኑን ክትባት ከወሰዱ በኋላ ያልተለመደ ነገር ግን እጅግ አደገኛ ሊሆን የሚችል የደም መርጋት መከሰቱን ተከትሎ ክትባቱ መሰጠቱ እንዲቋረጥ ተድርጓል። ከመካከላቸው አንደኛዋ ሴት መሞቷም ተዘግቧል።

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የጄ ኤንድ ጄውን ክትባት ሰባት ሚሊዮን ሰዎች የተከተቡት ሲሆን የተጠቀሰው ያልተለመደ የጎንዮሽ ችግር የተከሰተው ስድስቱ ላይ እንደሆነ ተመልክቷል።

የጆንሰን ኤንድ ጆንሰኑ የኮቪድ ክትባት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እየተሰጡ ካሉት ክትባቶች በቁጥሩ እጅግ አነስተኛው ቢሆንም ሰዉን መከተብ ላይ እንዲያመነታ ሊያደርገው ይችላል ብለው የጤና አዋቂዎች ይሰጋሉ።

የብሄራዊ የአለርጂና የተላላፊ በሽታዎች ተቋም ዳይሬክተሩ ዶ/ር አንተኒ ፋውቺ ጉዳዩን እየመረመረ ያለው የሲዲሲው ነጻ አማካሪ ኮሚቴ በዚህ ሳምንት በሚያደርገው ስብሰባ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰኑ ክትባት መሰጠቱ እንዲቋረጥ የተደረገውን ውሳኔ ያነሳል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የኮቪድ-19 መረጃ ማዕከል እንዳስታወቀው በዓለም ዙሪያ በኮሮናቫይረስ የተያዘው ሰው ቁጥር ዛሬ ከ142 ነጥብ 1 ሚሊዮን አልፏል። ከዚህ ውስጥ በበሽታው ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከሦስት ሚሊዮን ማለፉንም መረጃው ያመለከታል።

በዓለም ዙሪያ በኮሮናቫይረስ የሚያዘው ሰው ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአሜሪካውያን "እንዳትጓዙ" በሚለው ማሳሰቢያው ዝርዝር ውስጥ ያሉትን ቁጥር በሰማኒያ ከመቶ ከፍ ማድረጉን ትናንት አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG