በዩናይትድ ስቴትስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ለስድስት የምርጫ ዘመናት፤ ቀደም ሲልም በሕግ መምሪያው፤ በወጣትነት ዕድሜአቸውም ሃገራቸውን በውትድርና ያገለገሉት የሴናተር ጃን መክኬን አስከሬን ዛሬ ሜሪላንድ ዋና ከተማ አናፖሊስ ውስጥ ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ በተገኘበት የቀብር ሥነ-ሥርዓት አርፏል።
ለሴናተር መክኬን የተደረገው ለአምስት ቀናት የዘለቁ የመታሰቢያና የአሸኛኘት ሥነ-ሥርዓቶች በእንደራሴነት ባገለገሏት አሪዞና ግዛትና ዋና ከተማዪቱ ዋሺንግተን ዲሲ ውስጥም ከትናነት በስተያ በተወካዮች ምክር ቤቱ፤ ትናንትም በብሄራዊው ካቴድራል በመንግሥታዊ ክብር ተከናውነውላቸዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ባሕር ኃይል የጦር ጄት አብራሪና ተዋጊ፣ ለአምስት ዓመታትም በቪየትናም እሥር ቤት የበረታ ሥቃይ ያሳለፉት ጃን መክኬን ባለፈው ጥቅምት ወታደራዊ ዕውቀታቸውን ወደቀሰሙበት አካዳሚ ብቅ ያሉ ጊዜ ላገኟቸው የተማሪዎች መማክርት ጉባዔ አባላት ሲናገሩ ያኔ ወደፊት ይጠብቋቸው ለነበሩ እጅግ የከበዱ ፈተናዎች ትምህርት ቤታቸው ምን ያህል እንዳዘጋጃቸው አስታውሰውላቸዋል።
“በዚህ ሥፍራ የሠረፀብኝ የክብር ስሜት፣ እጅግ የጨለሙ ቀኖቼ በዋጡኝ ጊዜ እየመጣ ሹክ ይለኝ፣ ይናገረኝ ነበር። እናም አሁን ውርደትን እፀየፍ ዘንድ ወደተማርኩበት ወደዚህ ሥፍራ እንደገና፣ ደግሞም እንደገና እመላለሳለሁ።”
ለሙሉው ቅንብር የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ