በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አል ሸባብ በኢትዮጵያና ሶማሊያ ወታደሮች የጦር ግቢ ላይ ጥቃት ፈጸመ


የኢትዮጵያ ካርታ
የኢትዮጵያ ካርታ

አል ሻባብ በሶማሊያ የሚገኝ አንድ ወታደራዊ ሰፈርን ዛሬ ማጥቃቱን የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል። ሁለት የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ፍንዳታዎች የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ወታደሮች በሚገኙበትና ባርዴር በተሰኘችው ደቡባዊ ከተማ ባለ ወታደራዊ ሰፈር መፈጸሙን ምንጮች ተናግረዋል። ወዲያውም የከባድ መሣሪያ ተኩስ ተሰምቷል።

ጥቃቱ የተከሰተው የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል ወታደሮችን መቀነስ መጀመሩን ባስታወቀበት ወቅት ነው።

አል ሻባብ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን በወሰደበት ጥቃት ምን ያህል ጉዳት እንደደረሰ ወዲያውኑ ማወቅ እንዳልተቻለ ዘገባው አመልክቷል።

የመጀመሪያው ፍንዳታ የኢትዮጵያ ወታደሮች፣ የሶማሊያ ወታደሮችን በሚያሰለጥኑበት ግቢ መግቢያ በር ላይ እንደነበር የአካባቢው የፖሊስ አባል የሆነው አብዲ ባሬ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግሯል። ሁለተኛውም ፍንዳታ ከ5 ደቂቃ ቆይታ በኋላ እንደተስማና ተጎጂዎችም ሊኖሩ እንደሚችሉ፣ ነገር ግን ዝርዝር መረጃ እንደሌለ የፖሊስ አባሉ ጨምሮ ገልጿል። ከመጀመሪያው ፍንዳታ በኋላ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ እንደነበር ጨምሮ ተናግሯል።

ጥቃቱን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት እስከአሁን ያለው ነገር የለም።

ባለፈው ወር የአልሸባብ ተዋጊዎች የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ልዑክ ላይ ባደረሱት ጥቃት 54 የኡጋንዳ ወታደሮች መሞታቸው ይታወሳል፡፡

XS
SM
MD
LG